ኢትዮጵያ በሂደት እና በጋራ ጥረት የምትገነባ ሀገር እንጂ በአንድ ቀን የሚሳካ ተአምር እንደሌለ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአዲስ አበባ ሁለተኛ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለሀብቶች፣ ጡረተኞች፣ የመነገጃ ቦታቸውን መልሰው እንዲገነቡ የተገደዱ ዜጎች፣ ወጣቶች እና መላው የህብረተሰብ ክፍሎች የተሰማቸውን ጥልቅ ምስጋና አቅርበዋል።
ሀገር የምትሠራው በጋራ እና በሂደት መሆኑን ጠቅሰው፣ አዲስ አበባ አሁን ባለው ሁኔታ በምንም መመዘኛ ከየትኛውም ዓለም አቀፍ ከተማ ጋር ሲወዳደር የማያሳፍር ደረጃ ላይ መድረሷንና በቀጣይ ያልተሰሩ አካባቢዎችንም በማዳረስ ሙሉ ከተማውን ለዜጎች ምቹ ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዜጎች በንጹህ እና ምቹ ከባቢ አየር ውስጥ በመኖር በእግር መንቀሳቀስ መቻላቸው ለጤናማ ማኅበረሰብ ግንባታ ያለውን ፋይዳ ጠቅሰው፣ ከበሽታ በኋላ ሆስፒታል ከመገንባት ይልቅ አስቀድሞ ለጤና ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን መፍጠር፣ ዛፎችን መትከል እና ከተማውን አረንጓዴ ማድረግ እጅግ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ እጅግ አስደናቂ ለውጥ ለልጆቻችን ትልቅ ተስፋን የሚሰጥና ወደፊት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚገፋፋ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በአደይ አበባ ስታዲየም ጎን የዕውቁ አርበኛ እና የስፖርት ሰው የአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ሀውልት መቆሙን አስታውሰዋል።
የሰሩ እና ያገለገሉ አርበኞችንና ታላላቅ ሰዎችን ማስታወስ እና ምልክታቸውን ማስቀመጥ መጪው ትውልድ እነሱን እያዩ እንዲሻሻል እና የሀገር ስም እንዲያስጠራ ትልቅ አርአያ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: