Search

"ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው ድንቅ ስጦታ!" - ከእረኛው ካሊድ ግኝት እስከ 3 ቢሊየን ዶላር አመታዊ ገቢ

ረቡዕ ኅዳር 09, 2019 107

ኢትዮጵያዊው እረኛ ካሊድ ዛሬ ተነስቶ በወቅቱ የፍየሎቹ መፈንጫ በነበረችው ቦታ ያስተዋላት አረንጓዴ ቅጠልና ቀይ ብስል ፍሬ አሁን ላይ የዓለምን ታላላቅ ከተሞችን አድምቃ፣ የቢሊየኖችን ማለዳ ስታነቃ ቢያይ ኖሮ በመገረምና በኩራት "ያኔ በጫካ ያስተዋልኩት የፍየሎቼ ፈንጠዝያ ለካ የዓለምን ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅስ ታላቅ በረከት ኖሯል!" ሲል በሐሴት ይናገር ነበር።

ካሊድ ከዓለም ሁሉ አስቀድሞ ያገኛት ቡና ዛሬ ላይ ስሟ በዓለም ገንኖ፣ ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና ከሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ጋር ተዋህዶ ዓለምን ሲያስደምም ቢያይ ደግሞ መደነቁ እጥፍ ድርብ ይሆን ነበር።

ኢትዮጵያ ካሊድን አኩርታዋለች፤ ያኔ የጀመረውን ታሪክ ዛሬ ላይ የሀገራችን የኢኮኖሚ ሪፎርምና የመደመር እሳቤ አጠናክሮት፣ የኢትዮጵያ ቡና መገኛነት ከታሪክነት አልፎ ግዙፍ የልማት ምዕራፍ እና ተጨባጭ የኢኮኖሚ ዋልታ ከመሆን ላይ ደርሷል።

ኢትዮጵያ የባለልዩ ጣዕም ቡና መገኛ ብቻ ሳትሆን፤ ከሲዳማ እስከ ይርጋጨፌ፣ ከጅማ እስከ ሐረር፣ ከወለጋ እስከ ጉጂ የሚበቅሉ ልዩ ልዩ የቡና ዝርያዎች መፍለቂያ ናት፤ በጥራት አምርታም ለዓለም ገበያ የምታቀርብ ሀገር ሆናለች።

የመደመር መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረትና በዘረጋው የዲጂታል አሠራር፣ የአርሶ አደሩ ምርታማነት አድጎ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ያለው ተወዳዳሪነት በላቀ ደረጃ ማደግ ተችሏል።

በተለይም ሀገራችን ለሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂ በሰጠችው ልዩ ትኩረት፣ የኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት የቡና ምርታማነትንና ጥራትን ለማሳደግ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መፍትሔዎችን በመተግበር ላይ ይገኛል።

የቡና ተክል በሽታዎችን አስቀድሞ በመለየት፣ የአፈር ለምነትን በመተንተን፣ እንዲሁም የቡና ፍሬዎችን ጥራት በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመመዘን፣ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ያለውን ተዓማኒነትና ተፈላጊነት ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሮታል።

የዚህ የተቀናጀ የልማትና የቴክኖሎጂ ጉዞ ውጤት የሆነው ታሪካዊ ስኬትም በባለፈው በጀት ዓመት በደማቁ ተረጋግጧል።

ኢትዮጵያ ከቡና ኤክስፖርት 3 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት የያዘችው ታላቅ ዕቅድ በስኬት ተከናውኗል።

በሀገራችን ታሪክ ይህ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ የገቢ መጠን፣ የመንግሥት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲዎች ትክክለኛነት፣ የውጭ ምንዛሬ አቅማችንን የማጠናከር አቅም እንዲሁም የአርሶ አደሮቻችንንና የላኪዎችን ትጋት በግልጽ ያሳየ ደማቅ ድል ነው።

ይህ የኢትዮጵያ የልማትና የቡና ገናና ስም በቱርክ አንታሊያ እየተካሄደ ባለው የCOP31 ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይም በደማቁ ተንጸባርቋል።

በቱርክዬ አንታሊያ በተከፈተው የኢትዮጵያ ፓቪሊዮን ውስጥ፤ ባህላዊ የቡና ሥነ-ሥርዓት፣ የአረንጓዴ ዐሻራ ስኬቶችና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕድገቶች ተቀናጅተው ለዓለም አቀፍ እንግዶችና የቡና አስመጪዎች ቀርበዋል።

ሀገራችን ለቀጣዩ ዓመት የCOP32ጉባኤ በአዲስ አበባ ለማስተናገድ በምትዘጋጅበት በዚህ ወቅት፣ የኢትዮጵያ ቡና ታሪክን፣ ቴክኖሎጂንና ዘላቂ ልማትን አጣምሮ የሀገራችንን የብልጽግና ጉዞ በዓለም አደባባይ የሚያስተዋውቅ ዋነኛ መሳሪያ ሆኖ ቀጥሏል።

በልዩ እሸቱ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: