ለአፍሪካ እግር ኳስ መወለድና ማበብ የኢትዮጵያ አበርክቶ ከፍ ያለ ቦታ እንዲይዝ ምክንያት የሆኑት ኢትዮጵያዊው የስፖርት ሰው ‘የአፍሪካ የእግር ኳስ አባት’ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ከተማ ለሳቸው መታሰቢያ የተሰራው ሐውልት በይፋ ተመርቋል።
ጀግኖቿን በማስታወስ ያለማቋረጥ እንደስሟ እያበበች የምትገኘው መዲናችን ዛሬ ደግሞ በቦሌ የኮሪደር ልማት የታላቁን የስፖርት ሰው የአቶ ይድነቃቸው ተሰማን የመተታሰቢያ ሀውልት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) በተገኙበት ነው የተመረቀው።
ታላቅ የስፖርት ሰው የእግር ኳስ ተጨዋች፤ አሰልጣኝ፤ አስተማሪ፤ የቡድን መሪ፤ ኮሜንታተር፤ የስነ ልቦና ባለሙያ እና በተለያዩ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የስፖርት መድረኮች ፕሬዝዳንት ሆነው ያገለገሉት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ናቸው።
አቶ ይድነቃቸው ተሰማ መስከረም 1 ቀን 1914 ዓ.ም ከአባታቸው ከታዋቂው የሙዚቃ ሰው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መካኒክ፣ ሾፌር እና የስነ ጽሁፍ ሰው ከነጋድራስ ተሰማ እሸቴ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ሙላቷ ገብረስላሴ በጅማ ከተማ እንደተወለዱ ታሪካቸው ያሳያል።
አባታቸው ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ በልጅ እያሱ ጊዜ የቴሌግራፍ እና የፖስታ ሚኒስትር ሆነው በማገልገላቸው ቀዳማይ ኃይለስላሴ ስልጣን ሲይዙ በግዞት ወደ ጅማ በላኳቸው ጊዜ ነበር አቶ ይድነቃቸው እዚያው የተወለዱት።
የይድነቃቸው ተሰማ የስፖርት ዓለም ተሳትፎ የሚጀምረው ገና በ8 ዓመት ዕድሜያቸው የተፈሪ መኮንን ት/ቤት የህፃናት ቡድን ‘አምበል’ ሆነው ኳስ መጫወት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ነው።
ሁለገብ ስፖርተኛ የነበሩት ይድነቃቸው ተሰማ በአጭር ርቀት ሩጫ፣ በቦክስ እና በብስክሌት ስፖርተኝነትም የታወቁ ነበሩ።ከሁሉም በላይ ግን ታላቅ እግር ኳስ ተጫዋች የነበሩ ሲሆን ለክለባቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንድ የወድድር ዘመን 43 ግቦችን በማስቆጠር በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ አይረሴ እንደሚያደርጋቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
ከአቶ ይድነቃቸው ተሰማ አበርክቶዎች ዋና ዋናዎቹ፡-
⚽️አቶ ይድነቃቸው በ1936 ዓ.ም ትዳራቸውን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንንም መስርተዋል።
⚽️በዚሁ ዓመትም በሀገሪቱ የክለቦች ውድድር እንዲጀመር አድርገዋል።
⚽️የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድንን በመመስረት ‘አምበል’ በመሆን አገልግለዋል።
⚽️ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 15 ጊዜ ተሰልፈው ተጫውተዋል።
⚽️የመጀመሪያው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፀሐፊ ሆነው ሰርተዋል።
⚽️የኢትዮጵያ ስፖርት ኮንፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊም ነበሩ፤ የአለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንትም ሆነው አገልግለዋል።
⚽️የሮም፣ የቶኪዮ እና የሞስኮ ኦሎምፒኮች የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን መሪ ነበሩ።
⚽️በአፍሪካ ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በመስራችነት እና በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት ሰርተዋል።
⚽️በአፍሪካ የስፖርት ኮንፌዴሬሽኖች ህብረት ውስጥ በመስራችነት እና በፕሬዝዳንትነት
⚽️በአፍሪካ የብሔራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር ውስጥ በመስራች እና በክብር ፕሬዝዳንትነት
⚽️በአፍሪካ የስፖርት ሚኒስትሮች ካውንስል በቋሚ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት
⚽️በዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት
⚽️የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባልነት እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሆነው አገልግለዋል።
⚽️የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአህጉሩ ውጪ ከእስራኤል ጋር የማጣሪያ ጨዋታ ባደረገ ጊዜ ጨዋታውን ከቴል አቪቭ በቀጥታ በማስተላለፍ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ኮሜንታተርም ናቸው።
በዓለም አቀፍ የስፖርት ደረጃ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ በተጨዋችነት፣ በቡድን መሪነት፣ በአሰልጣኝነት የኢትየጵያን ብሄራዊ ቡድንን ይዘው ከ1940 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የአፍሪካ እና አውሮፓ ሀገሮች ተዘዋውረዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን ወክለው በዓለም አቀፍ የስፖርት ጉባዔ ላይ የተካፈሉት በ1949 ዓ.ም በሱዳን ካርቱም ከተማ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን መስራች ጉባዔ ላይ ነበር።
ከዚህ ጉባዔ በኋላ በአደራጅ ኮሚቴነት፣ በምክትል ፕሬዝዳንትነት እና በፕሬዝዳንትነት የአህጉሪቱን የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ለ30 ዓመታት በታላቅ ትጋት፣ ብልህነት እና ቆራጥነት ማገልገላቸውን ያዩ አውሮፓዊያን "የጅብራልተሩ አለት" ይሏቸዋል፤"ጅብራልተር" ማለት በደቡባዊ የአውሮፓና በሰሜናዊ አፍሪካ ሜድትራኒያን ባህር ዳርቻ አቅራቢያ የሚገኝ ኒውክለር የማይሰነጥቀው አለት ለማለት ተፈልጎ ነው።
"የአፍሪካ እግር ኳስ አባት" የሚል ስያሜ የተሰጣቸው የስፖርቱ ሰው አቶ ይድነቃቸው ተሰማ 11 ልጆችን አፍርተው በ1979 ዓ.ም በካንሰር ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ታሪካቸው ያሳያል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: