እንደ ጋና እና ቡርኪና ፋሶ ያሉ የአፍሪካ ሀገራት የሚታወቁበትን የሺያ ቂቤን የሚያስገኘው ዛፍ በኢትዮጵያም መኖሩን ሰምተን ከጋምቤላ ከተማ 37 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ኢታንግ ልዩ ወረዳ በኤልያ መንደር ተገኝተናል።
የኤልያ መንደር የሺያ ቂቤን በባሕላዊ መንገድ የሚያዘጋጁ ሴቶች በብዛት የሚገኙበት አካባቢ ነው።
የመንደሯ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ኦጆ ሞገር እንደሚሉት፥ በአካባቢው አጠራር ‘የዎዶ ቂቤ’ን በባሕላዊ መንገድ የማውጣት ሥራ አድካሚ በመሆኑ የአካባቢው ሴቶች ሥራውን በደቦ ይከውኑታል።
የሺያ ዛፍ ፍሬ ለመስጠት በርካታ ዓመታትን ይወስዳል። በተተከለ በ30ኛው ዓመት እያንዳንዱ ዛፍ እስከ 40 ኪሎ ፍሬ መስጠት የሚጀምር ሲሆን፤ አንዴ ምርት መስጠት ከጀመረ በኋላ ለ100 ተከታታይ ዓመታት ያለማቋረጥ ያንኑ የምርት መጠን መስጠቱን ይቀጥላል።
ባህላዊ የሺያ ቂቤ አወጣጥን በተመለከተ፥ ፍሬው ከዛፍ ላይ ከተለቀመ በኋላ የላይኛውን የፍሬውን ክፍል ለምግብነት በማዋል የውስጠኛው እንዲደርቅ ይደረጋል። የደረቀው ፍሬ እሳት ገባ እስኪለው ተቆልቶ ሴቶቹ ቅባቱ እስኪወጣ ድረስ እየተቀባበሉ በሙቀጫ ይወቅጡታል። በደንብ እስኪልም ከተወቀጠ በኋላ የፈላ ውሃ ውስጥ በመጨመር እሳት ላይ ተጥዶ ቂቤው ከላይ እስኪጠል እንዲንተከተክ ይደረጋል።
የአካባቢው ማህበረሰብ የሺያ ቂቤን ለምግብነት፣ ለመድሃኒትነት እንዲሁም ለውበት መጠበቂያነት ይጠቀሙበታል።
የባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት አቶ ብሩክ አሳዬ እንደገለፁት፥ የሺያ ቂቤ ባሕላዊ አወጣጥ አድካሚ በመሆኑ ሥራው በዘመናዊ ማሽን እንዲከናወን በማሰብ ተቋሙ ምርምር በማድረግ ላይ ነው።
የባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ካሳሁን ተስፋዬ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በሺያ ቅቤ ምርት ከፍተኛ የሆነ አቅም እንዳላት ጠቅሰው፤ ተቋሙ እያከናወነው ያለው የምርምር ሥራ ምርቱን ከግብዓቱ አንፃር አሁን ካለበት 20 ፐርሰንት ወደ 80 ፐርሰንት ማሳደግ የሚያስችል ነው ብለዋል።
የሺያ ቂቤ በኮስሞቲክስ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለው ሲሆን፤ በምግብ ኢንዱስትሪም በቸኮሌት እና በኬክ ዝግጅት በፍሌቨርነት ያገለግላል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ
#ጋምቤላ #ኤልያመንደር #ሺያዛፍ #ሺያቂቤ