Search

ሊቨርፑል የወለደው ኮኮብ ሪዮ ንጉሞሃ ማን ነው?

ማክሰኞ ነሐሴ 20, 2017 652

ቀድሞ ነገር በአሌክሳንደር ይሳቅ ዝውውር ግንኙነታቸው የሻከረው ኒውካስትል ዩናይትድ እና ሊቨርፑል ምሽት 4 ሰዓት ላይ ያደረጉት የፕሪሚየር ሊጉ 2ኛ ሳምንት ጨዋታ ሀይል የተቀላቀለበት እና የዕለቱን ዋና ዳኛ ደሲሞን ሁፐርንም የፈተነ ሆኖ ተጠናቋል፡፡
በውጥረት በተሞላው እና ባለሜዳዎቹ አንቶኒ ጎርደንን ገና በመጀመርያው ግማሽ በቀይ ካርድ ያጡበት ጨዋታ እስከ 99ኛው ደቂቃ ሁለት አቻ ቀጥሏል፡፡
2ኛውን ግማሽ ሙሉ በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫዎት የተገደዱት ኒውካስትሎች ከጨዋታው አንድ ነጥብ እንደሚያገኙ እርግጠኛ ቢሆኑም የባከነው ሰዓት ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ሲቀሩት ተቀይሮ የገባው ሪዮ ንጉሞሃ 100ኛ ደቂቃ ላይ የቀዮቹን የአሸናፊነት ግብ አስቆጠረ፡፡
ለመሆኑ ሪዮ ንጉሞሃ ማነው?
ከእግር ኳስ ጋር የተዋወቀው በቼልሲ ነው፡፡ በምዕራብ ለንደኑ ክለብ አካዳሚ ስምንት ዓመታትን አሳልፏል፡፡ ነገር ግን ከአንድ ዓመት በፊት ያደገበት ክለብ ሊያቆየው ባለመፈለጉ ወደ ሊቨርፑል እንዲያመራ ሆነ፡፡
አሰልጣኝ አርን ስሎት ለዚህ ታዳጊ በቅድመ ውድድር ጨዋታዎች ላይ ዕድል ሰጥተውታል፡፡
ያገኛቸውን ዕድሎች ሁሉ በሚገባ የተጠቀመው ሪዮ ንጉሞሃ በቅድመ ውድድር ጨዋታዎች ላይ ግብ ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ጨዋታን የሚረዳበት መንገድ እና ፍጥነቱ በትክክልም የወደፊቱ ልዩነት ፈጣሪ ሊሆን እንደሚቻል ለመገመት ከባድ አይሆንም፡፡
ከርቀት የሚሞክራቸው ጠንካራ ምቶቹ፣ ኳስን የሚገፋበት መንገድ፣ ተጫዋቾችን የሚያልፍበት ሁኔታ እና እንዲህ አይነት ብዙ ጫና ያለበት ትልቅ ጨዋታ ላይ ያሳየው በራስ መተማመን አንድ 17 ዓመት ካልሞላው ታዳጊ የሚጠበቅ ባይሆንም እሱ ግን አድርጎታል፡፡
የፊታችን አርብ 17 ዓመቱን የሚይዘው ሪዮ ንጉሞሃ በሁጎ ኢኪቲኬ፣ ሙሀመድ ሳላ እና ኮዲ ጋክፖ ለሚመራው የፊት መስመር ሌላ አማራጭ ሆኖ ተከስቷል፡፡
በተለይ ከዲየጎ ዦታ ድንገተኛ ህልፈት እንዲሁም ከሉዊስ ዲያዝ እና ዳርዊን ኑኔዝ ክለቡን መልቀቅ በኋላ ሌላ ጠንከራ የፊት መስመር መገንባት ለሚፈልጉት ሆላንዳዊው አሰልጣኝ በረከት ሆኖላቸዋል፡፡
ኑጉሞሃ በሊቨርፑል የ133 ዓመት ታሪክ ውስጥ ግብ ያስቆጠረ በእድሜ ትንሹ ተጫዋች ሆኗል፡፡
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ደግሞ ከጄምስ ቫግሀን፣ ጄምስ ሚልነር እና ዋይኒ ሩኒ በመቀጠል ከግብ ጋር የተገናኝ በዕድሜ ትንሹ 4ኛው ተጫዋች የሆነበትን ምሽት አሳልፏል፡፡
የዝውውር መስኮቱ ሊጠናቀቅ ቀናቶች ብቻ መቀርታቸውን ተከትሎ ሊቨርፑል አሌክሳንደር ይሳቅን የማግኝት ዕድሉ የጠበበ ቢሆን ሪዮ ንጉሞሃ የሚባል የተከላካዮች ፈተና የሆነ አማራጭ እንዳለው ግን አሳይቷል፡፡
በአንተነህ ሲሳይ