Search

በ7ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ በምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቀረቡ ሀሳቦች እና ጥያቄዎች፡-

ሓሙስ ኅዳር 17, 2019 37

1. የታክስ ገቢ አሰባሰብ አሁንም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆኑ ይነገራል። መንግሥት የታክስ ገቢውን ከሀገር ውስጥ ምርት አንጻር ከፍ ለማድረግ ግብ አስቀምጦ እየሠራ ቢሆንም፣ በንግዱ ማኅበረሰብ በኩል ግን የሚጠየቀው ታክስ ከአቅም በላይ እና የተጋነነ ነው የሚሉ ቅሬታዎች ይሰማሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የታክስ ማጭበርበርና ገቢን በሕገ-ወጥ መንገድ የመደበቅ ተግባራት በሰፊው ይስተዋላሉ። መንግሥት ይህንን ተቃራኒ ገጽታ እንዴት ይመለከተዋል?

2. ጤናማና ፍትሐዊ የሆነ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት በመዘርጋት የታክስ ግብን እውን ለማድረግ ምን አዳዲስ ስልቶችና እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው?

3. በታክስ አሰባሰብ ሂደት የሚታየውን ሌብነትና ብልሹ አሠራር ለመግታት እንዲሁም ጥብቅ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ምን ተጨባጭ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ?

4. የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ከመቅረፍ እና የኢኮኖሚ መረጋጋትን ከማረጋገጥ አንጻር እስካሁን ያበረከተው አስተዋጽኦ ምንድን ነው?

5. የሀገራችን ኢትዮጵያ የብድር ዕዳ የመክፈል አቅም በአሁኑ ወቅት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

6. የኢኮኖሚ ማሻሻያው ከሚያስገኛቸው አወንታዊ ገጽታዎች ባሻገር፣ በተለይ የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥን ተከትሎ ለሚነሱ የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበት ጫናዎች መንግሥት የሚሰጠው ማብራሪያ ምንድን ነው?

7. እነዚህን ስጋቶች ለማቃለልና ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ምንድን ናቸው?

8.በሕገ-መንግሥቱ መሠረት በየ10 ዓመቱ መካሄድ የነበረበት የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ባለመደረጉ የበጀት ድልድል፣ የልማት ዕቅድ እና የምርጫ ክልል ክፍፍል በግምታዊ መረጃ ላይ እንዲመሠረቱ አድርጓል። ይህንን ክፍተት ለመሙላት ቆጠራው የሚካሄድበት ቆራጥ የጊዜ ገደብ በፕሬዝዳንቱ ንግግርና በምክር ቤቱ ሞሽን ውስጥ ተካቶ እንዲጸድቅ እንጠይቃለን።

9. በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ እንዲሁም በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶችን በአስቸኳይ መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል። መንግሥት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ምን እየሠራ ነው?

10. የሚዲያ ተቋማትና ነፃው ፕሬስ የመንግሥትን ተጠያቂነት የሚያረጋግጡ፣ የሰብአዊ መብት ጥበቃን የሚያግዙ እና የፖለቲካ ምኅዳሩን የሚያሰፉ ተቋማት ሆነው እንዲሠሩ መንግሥት ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ እና ጉዳዩ በንግግሩ ውስጥ እንዲካተት እንጠይቃለን።

በመሐመድ ፊጣሞ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: