Search

ፓስፖርቱን፣ ወርቁን እና ገንዘቡን በእጇ ለማድረግ የተነሳች ኢትዮጵያ

ቅዳሜ ኅዳር 19, 2019 175

ሀብት የሚለካው በመያዝ ብቻ ሳይሆን በሚያመነጨው ገቢ እና በሚፈጥረው እሴት ነው። በመዝገብ ወይም በጥሬ መልክ ተቀምጦ የቆየ ሀብት ለባለቤቱ ጌጥ ሊሆን ይችላል፤ የልማት ጉልበት ግን የሚሆነው ሥራ ላይ ሲውል እና በዘመናዊ አስተዳደር ሲመራ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ማብራሪያ እንዳመለከቱት፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሀብት ከጥቂት ዓመታት በፊት ከነበረበት 2.6 ትሪሊዮን ብር ወደ 9 ትሪሊዮን ብር ከፍ ብሏል።

በሥሩ የሚገኙ የልማት ድርጅቶች ዓመታዊ ገቢም ከ788 ቢሊዮን ብር ወደ 3.1 ትሪሊዮን ብር ያደገ ሲሆን፣ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ለ72 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።

ይህ ዕድገት አዲስ ሀብት ከመፍጠር ባለፈ፣ ቀደም ሲል በተበታተነ መንገድ ይባክን የነበረውን ሀብት ወደ ሥርዓት በማስገባት እና በተጠያቂነት በመምራት የተገኘ ውጤት ነው።

የዓለም ባንክ ትንታኔ እንደሚያሳየውም የልማት ድርጅቶች በእጃቸው የሚገኙ መሬትን፣ መሣሪያዎችን እና ሌሎች ንብረቶችን ይበልጥ ሥርዓት ባለው መንገድ መገምገም መጀመራቸው በመዝገብ የሚንጸባረቀውን ዋጋ እንዲያድግ አድርጓል።

ያልተቆጠረ ሀብት በጸጥታ ይባክናል፤ የተቆጠረ እና በአግባቡ የተመዘገበ ሀብት ግን ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን ያሰፍናል።

የዚህ የሪፎርም ምዕራፍ ትልቁ ስትራቴጂካዊ ፋይዳ የሚታየው ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን እና ተጠቃሚነቷን በቀጥታ የሚወስኑ ሦስት መሠረታዊ መስኮችን በራሷ እጅ ማጠናከር በመጀመሯ ነው።

ፓስፖርት የዜጎችን ማንነት የሚያረጋግጥ ሰነድ ሲሆን፣ ገንዘብ የእሴት መለኪያ ነው፤ ወርቅ ደግሞ ዋጋ የሚቀመጥበት እና የውጭ ምንዛሪ የሚገኝበት ስትራቴጂካዊ ማዕድን ነው።

እነዚህ መሣሪያዎች በውጭ አካላት እጅ ሲሆኑ የደንበኝነት ጥገኝነት ይፈጥራሉ፤ ሉዓላዊነትን ያጎድላሉ፡፡ በኢትዮጵያ እጅ ሲሆኑ ግን የባለቤትነት እና የሉዓላዊነት ጥንካሬን ያረጋግጣሉ።

ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ፓስፖርት በውጭ ሀገር ማሳተሟ የዜጎችን መረጃ እና የዳታ ሉዓላዊነት አሳልፎ ከመስጠት ጋር የተያያዘ ፈተና ነበረው።

ይህን ችግር ለመፍታት የተመሠረተው ቶፓን ሴኩሪቲ ኢትዮጵያ የሽርክና ኩባንያ፣ የጃፓኑ ቶፓን 51 በመቶ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በሥሩ ያሉ ሁለት ድርጅቶች 49 በመቶ ድርሻ ያላቸው ሲሆን፣ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ዞን በ55 ሚሊዮን ዶላር የተገነባው ፋብሪካ የፓስፖርት ሕትመትን በሀገር ውስጥ ያከናውናል።

ይህ እርምጃ የዳታ ሉዓላዊነትን ከማስጠበቁ በተጨማሪ የቴክኖሎጂ ሽግግርን እና የሀገር ውስጥ አቅም ግንባታን ያፋጥናል። ለሌሎች ሀገራት በማተምም የውጭ ምንዛሬን ያስገኛል፡፡

በወርቅ ዘርፍም በጥቅምት ወር የተመረቀው የመጀመሪያው የወርቅ ማጣሪያ በ50 ሚሊዮን ዶላር መነሻ ኢንቨስትመንት የተቋቋመ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የ51 በመቶ ባለቤትነት ድርሻ ይዟል።

በቦሌ ለሚ ልዩ ኢኮኖሚያዊ ዞን የሚገኘው እና ዓመታዊ ከ600 ቶን በላይ የከበሩ ማዕድናትን የማጣራት አቅም ያለው ይህ ተቋም፣ ባለፈው ዓመት ከወርቅ የተገኘውን 5.6 ቢሊዮን ዶላር የኤክስፖርት ገቢ በማሳደግ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

ከኢትዮጵያም ሆነ ከጎረቤት ሀገራት የሚመጣን ወርቅ በማጣራት ከጥሬ ወርቅ ሽያጭ ወደ ተጣራ ወርቅ መሸጋገር መቻሉ ኢትዮጵያ ከሀብቷ የምታገኘውን እሴት እና የውጭ ምንዛሪ ተጠቃሚነት በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል።

የገንዘብ ሕትመትን በኢትዮጵያ ውስጥ የማስፋፋት እና የማጠናከር ዕቅድም የዚሁ ሰፊ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ስትራቴጂ አካል ነው።

ኢትዮጵያ ሀብቷን በአግባቡ በመቆጣጠር፣ በሀገር ውስጥ እሴት በማከል እና ስትራቴጂያዊ ዘርፎችን በራሷ እጅ በማጠናከር ዘላቂ የብልጽግና እና የሉዓላዊነት መስመር ላይ ትገኛለች።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: