Search

ብርሃኗ ከራሷ አልፎ ለጎረቤት የሚተርፍ ኢትዮጵያ

ቅዳሜ ኅዳር 19, 2019 149

ኢትዮጵያ የጀመረችው አዲስ የልማት ምዕራፍ ከድንበሯ አልፎ ለመላው የአፍሪካ ቀንድ የጋራ ተስፋ እና የብልጽግና መሠረት እየጣለ ነው።

ታሪክ እና ጂኦግራፊ ኢትዮጵያን የቀጣናው የትስስር ማዕከል አድርገው ፈጥረዋታል። ይህን ተፈጥሯዊ ስጦታ ወደ ተግባራዊ ልማት የሚቀይሩ የመሠረተ ልማት፣ የኃይል፣ የትራንስፖርት እና የዲጂታል ፕሮጀክቶች ጎረቤት ሀገራትን በመተማመንና በመደጋገፍ እያስተሳሰሩ ነው።

ድንበሮች የመለያያ መስመር መሆናቸው ቀርቶ ገበያ፣ ኃይል እና ሰላም የሚጋሩባቸው መድረኮች እየሆኑ ነው።

የኃይል ትስስር ይህን በተጨባጭ ያሳያል። የህዳሴ ግድብ 5 ሺህ 150 ሜጋዋት እያመነጨ የኢትዮጵያን የኃይል አቅም ከእጥፍ በላይ አሳድጓል።

በ2018 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ 2 ሺህ 497 ጊጋዋት ሰዓት ኤሌክትሪክ ወደ ጎረቤት ሀገራት ልካለች፡፡

ከዚህ ውስጥ ኬንያ 1 ሺህ 589፣ ጂቡቲ ደግሞ 546 ጊጋዋት ሰዓት ተጠቅመዋል። ታንዛኒያም በሙከራ ደረጃ 100 ሜጋዋት እያገኘች ነው።

ለኬንያ የሚቀርበው ኃይል  ከ200 ወደ 400 ሜጋዋት ያድጋል። ይህ ኤሌክትሪክ የጎረቤቶችን ኑሮ በቀጥታ የሚያቃልል ሲሆን፣ አንዱ ሲበለጽግ ሌላው አብሮ የሚያድግበትን ፍልስፍና በተግባር እያጸና ነው።

የቀጣና መሪነት በጋራ ፈተናዎች ፊት ግንባር ቀደም ሆኖ መቆምን እና ለዘላቂ መፍትሔ መሥራትንም ያካትታል።

ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር፣ በዲፕሎማሲ እና በቀጠናዊ ውህደት ያላትን ልምድ ተጠቅማ የአካባቢውን መረጋጋት የምታስጠብቀው የጎረቤቶቿን ሰላም የኔ ሰላም ነው ብላ ስለምታምን ነው። በዚህ ጉዞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ልዩ ስፍራ አለው።

ኢትዮጵያ የተመድ ሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ቀዳሚ አስተዋጽዖ አበርካች ነች። ሠራዊቷ ለሉዓላዊነት እና ለሀገሩ ሕልውና ከመቆም ባለፈ፣ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ሰላም እንዲሰፍን የከፈለው መስዋዕትነት የኢትዮጵያን ቀጣናዊ ኃላፊነት በተግባር አረጋግጧል።

አቅሙ እየተገነባ ያለው መከላከያ ሠራዊት የጋራ ደኅንነትን በማረጋገጥ ረገድ ዋነኛ ምሰሶ ሆኖ ይቀጥላል።

ኢትዮጵያ በራሷ እምቅ አቅም የምትተማመን፣ ለሌሎች በር ከፋች እና አጋር ሀገር ናት።

ከድንበር ባሻገር የሚተርፍ አቅምና በጎ ራዕይ ይዞ መንቀሳቀስ የቀጣናውን የነገ ታሪክ በአዲስ መልክ የሚጽፍ፣ ክብርን እና ብልጽግናን የሚያረጋግጥ እውነተኛ የመሪነት መንገድ ነው።

በሔዋን ጌታቸው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: