Search

ቡናው ሲፈላ ምክክሩ ይጀምራል፡ ጅማ እንግዶቿን የምትቀበልበት ዘይቤ

ቅዳሜ ኅዳር 19, 2019 118

በጅማ  የመጀመሪያው ሲኒ ቡና  ከመቀዳቱ በፊት ጸሎት ይቀድማል። የተቆላው ቡና መዓዛ ቤቱን ሲሞላ ተሰብሳቢው በአንድነት "ሰላም ስጠን" ይላል።

ታላላቆች ደግሞ ቡና እና ሰላም እንዲሰፍን፣ ቤትና ጎረቤት እንዲያምር ይመርቃሉ። የራስ ቤት መልካም ምኞች ከጎረቤት ውበት ጋር በአንድ ምርቃት ውስጥ የሚጠራበት ይህ ልማድ ብዝኃነት የመድረክ ቃል ብቻ ሳይሆን የዕለት ተዕለት ኑሮ መሆኑን ያሳያል።

ኅዳር 29 ቀን 2019 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን በ"ብዝኃነት የደመቀች፣ በምክክር የጸናች ሥልጡን ኢትዮጵያ!" መሪ ቃል 21ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ለማክበር ወደ ጅማ ያመራሉ።

ጅማ ከታሪካዊነቷ ባሻገር ዛሬ ደግሞ በኮሪደር ልማት ውበትን ተላብሳለች፤ ምክክርን ከመድረኩ በፊት በጀበናዋ ዙሪያ የኖረች ከተማ መሆኗም የጅማ መገለጫዋ ነው።

ይህ ታሪክ ሥር ሰዶ የቆየ ነው። ከጊቤ መንግሥታት መካከል በኃይል እና በብልጽግና የገነነው የጅማ መንግሥት፣ በንጉሥ ዳግማዊ አባ ጅፋር (1878–1932) ዘመን በንግድ፣ በዲፕሎማሲ እና በትምህርት ይታወቅ ነበር።

ንጉሡ ከንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ጋር በድርድር የመንግሥታቸውን ራስ ገዝነት አስጠብቀዋል። በዘመናቸው የቡና እርሻ እና ንግድም ተስፋፍቷል።

የምዕራብ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ነጋዴዎችን ያገናኝ የነበረው ገበያ፣ ሊቃውንትን እና ተማሪዎችን ያስተናገዱት የጂሬን መድረሳዎች፣ በ1880ዎቹ በጂሬን ኮረብታ ላይ የታነጸው የንጉሡ ቤተ መንግሥት የዚህ ማሳያዎች ናቸው። ጅማ ሰውን ከእንግድነት ወደ ቤተኛነት የምታሻግር ከተማ ነበረች።

በዚህ ታሪክ ውስጥ ምክክር እንዴት ይሠራ ነበር? ብለን ብንጠይቅ መልሱ በቡና ባህሏ ውስጥ አለ። በጅማ ቡናን በሥነ ሥርዓት አፍልቶ በዙሪያው ተሰብስቦ መወያየት የኖረ ባህል ነው። ቡናው ሲቀዳ ንግግሩም ይጀምራል፣ ይረጋጋል፣ ይደመደማል።

ከቡናው ጋር ቁርስ መቅረቡ ግዴታ ነው፤ ማኅበረሰቡም "ቁርስ የሌለው ቡና መደምደሚያ እንደሌለው ንግግር ነው" ይላል።

በቡና ሥነ ሥርዓቱ  የሚቋደሱት ቡናዉንና  ቁርሱን  ብቻ አይደለም፤ የሰላም እና የአብሮነት ቃል ኪዳንም ጭምር ነው። ዘግይቶ ለመጣ እንግዳ እንኳ ሲኒው ተቀምጦለታል፤ ማንም በመዘግየቱ አይጎድልበትም።

እንደ ቡና  ሥነሥርዓቱ የአዌቱ ወንዝ ዳርቻ መናፈሻዎችም ተውበው እንግዶቻቸውን እየጠበቁ ነው። የከተማው ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የኮሪደር ልማቱ የጎብኚዎችን ቁጥር እንዳሳደገ ገልጿል።

ኅዳር 29 እንግዶች በአዲሱ መንገድ ይራመዳሉ። ከበዓሉ በኋላ ግን የሥልጡን ኢትዮጵያ መለኪያ የሆነው ጥያቄ ይቀራል፦ ሲኒው ዞሮ ሲያበቃ ለሁሉም ደርሷል ወይ? ጅማ ይህን ጥያቄ ስትመልስ የኖረችው በጀበናዋ ዙሪያ ነው። ይህን ውብ ባህሏን ለእንግዶቿ ስንቅ አድርጋ ትሸኛለች፡፡

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: