Search

“በሚቀጥለው ዓመት ለCOP32 ከ100 ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን በብቃት እና በጥራት ለማስተናገድ እየተዘጋጀን ነው” - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ቅዳሜ ኅዳር 19, 2019 172

አዲስ አበባ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ30 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የታደሙበትን ታላቅ አህጉር አቀፍ ኮንፈረንስ በብቃት ማስተናገዷን የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።

ከንቲባዋ በመልዕክታቸው ከ30 ሺህ በላይ የሚሆኑት የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ለተከታታይ ስድስት ቀናት በአዳራሽ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመዲናዋ የተለያዩ ስፍራዎች እየተዟዟሩ መጎብኘታቸውን አስታውቀዋል።

እንግዶቹ በቀን ብቻ ሳይሆን በምሽት እና በሌሊት ጭምር በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ በነፃነት እየተዟዟሩ መዝናናታቸውን እና ለከተማዋ ያላቸውን አድናቆት መግለጻቸውን ጠቁመዋል።

ይህ ስኬት አዲስ አበባ ትልልቅ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ዝግጅቶችን በብቃት፣ በጥራት እና በኃላፊነት ማስተናገድ የምትችል ከተማ መሆኗን በተግባር ያረጋገጠ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ታላቁን ኮንፈረንስ ላዘጋጀው የአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) እንዲሁም ዝግጅቱን በዋናነት ላስተባበረው የጤና ሚኒስቴር ምስጋና አቅርበዋል።

ከዚህም ባለፈ እንግዶችን በመቀበል እና በማስተናገድ፣ በትራንስፖርት፣ በሆቴል፣ በውኃ፣ በመብራት፣ በአዳራሽ አገልግሎት፣ በጸጥታ፣ በማስጎብኘት፣ በጽዳት እና በሌሎችም ዘርፎች የተሳተፉ ሁሉም ተቋማት እና የሥራ ኃላፊዎች ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

አዲስ አበባ በሚቀጥለው ዓመት ለሚካሄደው የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) ከ100 ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን በብቃት እና በጥራት ለማስተናገድ እየተዘጋጀች መሆኗን ከንቲባዋ ገልጸዋል።

ለዚህም ከአሁኑ ጀምሮ ልዩ ትኩረት በመስጠት በእጅ ያሉ ሥራዎችን በጊዜ፣ በጥራት እና በብቃት መፈጸም እንደሚገባ አሳስበዋል።

ይህንን ታላቅ ዕድል ሳያባክኑ የኢትዮጵያን የእንግዳ ተቀባይነት፣ የፈጠራ አቅም እና የሥራ ትጋት ለዓለም በተግባር ማሳየት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

COP32ን ውጤታማ እና የማይረሳ ታላቅ ዓለም አቀፍ ዝግጅት ለማድረግ ዛሬ በትጋት በመሥራት ዓለምን በመዲናችን አስተናግደን ኢትዮጵያን በኩራት እናሳይ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: