የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር ባለፉት 45 ቀናት ውስጥ ፈርሶ የነበረውን የክልሉን መዋቅር መልሶ በማደራጀት፣ በጀት መድቦ መስራትና ሕግ ማስከበር የሚችል የመንግሥት ቁመና ላይ መድረሱን የባለአደራ አስተዳደሩ የአስተዳደርና የሕዝብ አገልግሎት ዋና አስፈፃሚ አቶ አሰፋ አብረሃ ልጸዋል።
ባለአደራ አስተዳደሩ የ45 ቀናት የሥራ አፈጻጸም ግምገማውን ዛሬ በአዲስ አበባ አካሂዷል። ከዚህ ቀደም የመጀመሪያው ግምገማ ከሦስት ሳምንታት በፊት በመቐለ መካሄዱ ይታወሳል።
ባለፉት 45 ቀናት ተበትኖ የነበረውን አስተዳደር መልሶ የማቋቋም ሥራ በስፋት መከናወኑን አቶ አሰፋ ተናግረዋል።
ከቀበሌ እና ከወረዳ ምርጫዎች በመነሳት አዳዲስ የባለአደራ አመራሮች የተመረጡ ሲሆን፣ የዞን አመራሮች እና የተሟላ ክልላዊ ካቢኔ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል።
ከመዋቅር ግንባታው ጎን ለጎን የፍትሕ፣ የዳኝነት፣ የፖሊስ እና የሚሊሻ አደረጃጀቶች እንዲጠናከሩ መደረጉን አቶ አሰፋ ጠቅሰዋል።
በዚህም ከእስር ቤት ወጥተው የከተሞችን ሰላም ሲያውኩ በነበሩ የወንጀል ቡድኖች ላይ እርምጃ በመውሰድ በርካታ ከተሞችን ከወንጀል ሥጋት ነጻ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።
የመንግሥት ቁመናውን ይበልጥ ለማጠናከር በቀጣይ ዙር በልዩ ትኩረት የሚከናወኑ አራት ዋና ዋና አቅጣጫዎችም መቀመጣቸውን አመልክተዋል።
የተመደቡ አመራሮችን በበጀት እና በተግባር መፈተን፣ ተፈናቃዮችን በቅድሚያ ወደ ቀያቸው መመለስ፣ በደቡብ ትግራይ፣ በምሥራቅ እና በተምቤን የተከሰተውን ከባድ ድርቅ ተከትሎ በእርዳታ በመቋቋም የሰውን ሕይወት መታደግ እንዲሁም በስድስት ወሩ ማብቂያ ላይ በሕዝብ ለተመረጠ መንግሥት ሰላማዊ ሽግግር የሚደረግበትን ምርጫ ማካሄድ ቀጣይ ተግባራት መሆናውን አቶ አሰፋ ጠቁመዋል።
የአመራር አካላቱ በ45 ቀናት ውስጥ በተመዘገበው ውጤት ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ለቀጣይ ሥራዎች የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እና ድጋፎች እንደሚቀርቡ አረጋግጠዋል።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: