ኢትዮጵያ ለወዳጆቿ የሰላም እና የወንድማማችነት ጥላ፣ ለሉዓላዊነቷ ፈተና ለሆኑ ኃይሎች ግን የማትደፈር ጽኑ ምሽግ ናት።
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በዓድዋ ተራሮች የተመዘገበው አኩሪ ድል ኢትዮጵያን ከቅኝ ግዛት ከመታደግ ባለፈ፣ ለመላው የአፍሪካ እና የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ብርሃን እና ተምሳሌት አድርጓታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባስተላለፉት መልእክት "ትንሽም ይሁን ትልቅ ማንም ኢትዮጵያን ወርሮ በክብር መመለስ አይችልም፤ ዓድዋ ይደገማል" ማለታቸው፣ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጽናት እና የሕልውና ቁርጠኝነት በግልጽ ያሳያል። ኢትዮጵያ በልጆቿ መሥዋዕትነት እና በሕዝቧ አንድነት ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎችን ተሻግራ ዛሬም በክብር ቆማለች።
የኢትዮጵያ ጥንካሬ በትናንት ታሪክ ብቻ የተገደበ አይደለም። በታዳሽ ኃይል፣ በግብርና፣ በመሠረተ ልማት እና በዲጂታል ሥርዓቶች የሚከናወነው የራስን አቅም የመገንባት ጉዞ የውጭ ጫናዎችን የመቋቋም አቅምን ከፍ አድርጓል።
በኢትዮጵያውያን ዕውቀት፣ ጉልበት እና ሀብት የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የዘመናችን የኅብረት ድል ማሳያ ነው።
ከ5 ሺሕ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት ከማፋጠን ባሻገር፣ ለጎረቤት ሕዝቦችም የጋራ ልማትና ትስስር መሠረት ሆኗል።
በበጋ መስኖ እና በመደበኛ እርሻ በስንዴ ምርት የተመዘገበው ስኬት ኢትዮጵያን ከውጭ እርዳታ እና ከስንዴ ግዥ ጥገኝነት በማላቀቅ በምግብ ራስን የመቻል ጉዞዋን አረጋግጧል።
ይህ የኢኮኖሚ ነጻነት የፖለቲካና የታሪክ ሉዓላዊነትን ይበልጥ የሚያጸና ነው። በራስ አቅምና ሀብት መቆም የውጭ ጣልቃ ገብነትን በማስቀረት በራስ መተማመንን የሚያጎለብት የኢትዮጵያ ክብር ዋና መሠረት ነው።
ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሕዝቦች ሰላም እና ለቀጣናው የጋራ ብልጽግና ቅድሚያ የምትሰጠው ከኃላፊነት እና ከወንድማማችነት መርሕ በመነሣት ነው።
ሰላምን እና ውይይትን መምረጥ የሉዓላዊነትን ዋጋ አይቀንስም፤ ትብብር እና ቅንነት የጥንካሬ እንጂ የድክመት መገለጫ አይደሉም።
ሆኖም የሰላም ጥሪን እንደ ድክመት ቆጥሮ የኢትዮጵያን ድንበርና ሉዓላዊነት ለመፈታተን የሚሞክር ማንኛውም ኃይል የዓድዋን ገድል በተባበረ ክንድ ተደግሞ እንደሚያይ ታሪክ ምስክር ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩም መልእክት ይኸው ነው።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: