የኢትዮጵያውያን የጥንት ሥልጣኔ ማሳያ የሆነው የአክሱም ሐውልት፣ በዕድሜ ብዛት ምክንያት ጉዳት እየደረሰበት ነው።
ቀደም ሲል ከጣሊያን መንግሥት ጋር በተደረጉ ስምምነቶች ውስን የጥገና ሥራዎች ቢከናወኑም፣ ቅርሱ አሁን የገጠመው ስጋት ልዩ ትኩረት እንደሚሻ ተመላክቷል።
በአካባቢው በሚገኙ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶች ላይ ጥናትና ምርምር የሚያደርገው የአክሱም ዩኒቨርሲቲ፣ የኅዳር ጽዮን የንግሥ በዓልን አስመልክቶ ሲምፖዚየም አዘጋጅቷል።
በሲምፖዚየሙ አራት ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ አመራሮች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
በመድረኩ ከጣሊያን መንግሥት ጋር የተጀመረው የሐውልቱ ጥገና ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምክረ ሐሳብ ቀርቧል።
ይህን ለማሳካትም የቱሪዝም ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን በቅንጅት እና በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ ተጠቁሟል። የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሀጎስ አብረሃ (ዶ/ር) በአክሱም ከተማ ዘላቂ የቅርስ ልማት ሥራ በቀጣዩ ሳምንትእንደሚጀመር ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም እንዳብራሩት፣ በጥንት ዘመን አክሱምን፣ ፋሲልን እና ላሊበላን ስንገነባ የተጠቀምነው እሴት "መደመር" ነው። በኢትዮጵያ የምናየው ታላቅ የታሪክ ውጤትም የእያንዳንዱ ሕዝብ የደም ጠብታ ድምር ነው።
ከዚህ ታሪካዊ አብሮነት ውጪ የተሠራ ፋሲልም ሆነ አክሱም እንደሌለ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ትናንት ተደምረን ታሪክ እንደሠራን ሁሉ ዛሬም ያሉብንን ፈተናዎች ተሻግረን የተሻለች ኢትዮጵያን መፍጠር የምንችለው በመደመር መንገድ ብቻ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
በአስማረ ብርሃኑ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: