Search

ዲጂታል ሉዓላዊነት የሚጀምረው ከትምህርት ቤት ደጃፍ ነው

ቅዳሜ ኅዳር 19, 2019 178

ዓለም በአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ውስጥ እየተራመደች ባለችበት ወቅት፣ የሰው ልጅ የመማር፣ የመሥራት እና የመገናኘት መንገዶች በቴክኖሎጂ እየተቀየሩ ናቸው።

የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና የዲጂታል ፈጠራዎች ተጽዕኖ ወደ ትምህርት ቤቶችም በስፋት በመግባቱ፣ የትምህርት ሥርዓቱ ከባህላዊ የአሠራር ልማድ ወጥቶ የዘመኑን ፍጥነት መቀላቀል ግድ ይለዋል።

በዚህ ፈጣን ለውጥ ውስጥ ዲጂታል መሠረተ ልማትን መጠበቅ እና ዲጂታል ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ ነው።

ይህ ራዕይ እውን የሚሆነው በንድፈ ሐሳብ ዕውቀት ብቻ ሳይሆን፣ በተግባራዊ ክህሎት፣ በፈጠራ እና በዲጂታል ኃላፊነት የታነጸ ብቁ ትውልድ ሲገነባ ነው።

ለዚህም የዲጂታል የፈተና ሥርዓት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታኅሣሥ 11 ቀን 2018 ዓ.ም ይፋ የተደረገው "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂ፣ ቀዳሚው "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" የጣላቸውን መሠረቶች የሚያጸና እና የተማሪዎችን ምዘና በዲጂታል በማካሄድ የብሔራዊ ፈተናዎችን ደኅንነት፣ ፍትሐዊነት እና ተዓማኒነት ይበልጥ የሚያሰፋ ነው።

የብሔራዊ ፈተናዎችን አፈጻጸም ከ90 በመቶ በላይ ወደ ዲጂታል መድረክ ማሸጋገር፣ ባለፉት ዓመታት የተገኙ ተሞክሮዎችን በማቀናጀት ምዘናን ፈጣን፣ ግልጽ እና አስተማማኝ ለማድረግ የሚያስችል ትልቅ እርምጃ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ፣ በዚህ ዓመት ቢያንስ 90 በመቶ የሚሆነውን ፈተና በበይነ መረብ ለመስጠት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዕውቀት፣ ፈጠራ እና ቴክኖሎጂ የኢትዮጵያን እምቅ አቅም የሚያንቀሳቅሱ ዋና ምሰሶዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) እና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ያቋቋመው የሰው ሠራሽ አስተውሎት የፈጠራ ማዕከል (AI UniPod) ለወጣት ፈጣሪዎች እና ሥራ ፈጣሪዎች የምርምር እና የፈጠራ መድረክ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲም በቅርቡ ሥራ ይጀምራል።

እነዚህ የምርምር፣ የፈጠራ እና የትምህርት ሥርዓት ማሻሻያዎች ሲቀናጁ፣ ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ብቻ ከመሆን ወጥታ የቴክኖሎጂ ፈጣሪ እና ባለቤት የምትሆንበት ምቹ መደላድል ይፈጠራል።

በዕውቀት የበለጸገ፣ በፈጠራ የታነጸ እና በኃላፊነት የሚመራ ትውልድ መፍጠር ኢትዮጵያ በአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ውስጥ ተመልካች ሆና እንዳትቀር እና ዲጂታል ሉዓላዊነቷን እንድታጸና የሚያስችል ጽኑ መሠረት ነው።

በሔዋን ጌታቸው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: