በምሥራቅ አፍሪካ እና በአፍሪካ ቀንድ ኢትዮጵያ ከታሪክ፣ ከሕዝብ ብዛት፣ ከጂኦ-ፖለቲካዊ አቀማመጥ እና ከልማት ትስስር አንጻር የማይተካ ስትራቴጂያዊ ቦታ አላት።
በ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በአፍሪካ ከናይጄሪያ ቀጥሎ ሁለተኛዋ ብዙ ሕዝብ ያላትና ታላቅ ምድር በመሆኗ፣ በኢትዮጵያ የሚፈጠር መረጋጋትም ሆነ መናወጥ በቀጥታ በጎረቤት ሀገራት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።
የኢትዮጵያ ጥንካሬ ቀጣናውን ለማስተሳሰር እና ለማረጋጋት ሲውል፣ ኢትዮጵያ ስትታወክ ግን የቀውሱ ወላፈን በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ ብቻ ተወስኖ የማይቀር ይሆናል።
ይህንን የኢትዮጵያን ግዝፈት እና ቀጣናዊ ክብደት ለማስገንዘብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት ጥያቄ የትንታኔው ዋና ማጠንጠኛ ነው።
"አሥር ሚሊዮን ኢትዮጵያዊ ወደ ኤርትራ፣ ዐሥር ሚሊዮን ወደ ሶማሊያ፣ ዐሥር ሚሊዮን ደግሞ ወደ ደቡብ ሱዳን ቢሄድ ምን ይፈጠራል?" የሚለው ጥያቄ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው ለማስፈራራት ሳይሆን፣ የሕዝብን መጠን እና የመዛባትን አደጋን ለማሳየት ነው።
መልሳቸውም አጭርና ግልጽ ነበር፤ እነዚህ ሁሉ ሰዎች በሚሄዱበት ቦታ ካለው አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር ይበልጣሉ የሚል ነው።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ኢትዮጵያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን አስጠልላ ትገኛለች።
አብዛኞቹ ከደቡብ ሱዳን፣ ከሶማሊያ እና ከኤርትራ የመጡ ሲሆኑ፣ ከሱዳን አሁንም በግጭቱ ምክንያት በርካታ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ይገኛሉ።
በዚህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞች በማስተናገድ በግንባር ቀደምት ተርታ ትገኛለች።
ጎረቤቶች ሲታወኩ የሰብዓዊነት ሸክሙን በግንባር ቀደምትነት የምትሸከመው ኢትዮጵያ ናት፤ ኢትዮጵያ ብትታወክ ግን ይህን ግዙፍ ሸክም ሊሸከምላት የሚችል ጎረቤት በቀጣናው የለም።
የኢትዮጵያ ቀጣናዊ ተፈላጊነት በሰብዓዊ መስተንግዶ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን፣ በታሪክ፣ በዲፕሎማሲ፣ በሰላም ማስከበር እና በዘመናዊ የልማት ትስስር የተረጋገጠ ነው።
ከቅኝ ግዛት ነፃ ሆና በመቆየቷ ለመላው አፍሪካውያን የነፃነት ፋና ወጊ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ዛሬም የአፍሪካ ሕብረት እና የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በመሆን ታገለግላለች።
በሰላም ማስከበር ረገድም የተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮዎች ከመጀመሪያዎቹ ተሰላፊዎች አንዷ ነበረች፤ አሁንም በቀጣናውም ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የራሷን አስተዋጽኦ እያበረከተች ትገኛለች።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና በሌሎች የኃይል ማመንጫዎች ለጎረቤት ሀገራት ንጹሕ ኃይል በማቅረብ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በባቡር እና በመሠረተ ልማት አውታሮች ቀጣናውን በማስተሳሰር የምሥራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ትስስር ማዕከል ሆናለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህንን እውነታ "ትልቅ ዛፍ ስለሆንን ከጸናን ጥላችን ሠፈሩን ያዳርሳል፤ ግንዳችን ከተጎዳ ግን ሁሉም ይጎዳል" በሚል ምሳሌ ገልጸውታል።
የኢትዮጵያ መረጋጋት እና መጽናት የቀጣናው ሀገራት የጋራ የህልውና ዋስትና ነው። የኢትዮጵያን ሰላም፣ አንድነት እና የልማት አቅም መጠበቅ ለኢትዮጵያ ዜጎች ብቻ ሳይሆን በጥላዋ ሥር ለሚጠለሉ፣ በኃይል እና በመሠረተ ልማት ትስስሯ ለሚጠቀሙና በሰላሟ ለሚረጋጉ ጎረቤቶች ሁሉ የጋራ ኃላፊነት ነው።
ግንዱ ሲጸና ቀጣናው ይጠቀማል፤ ግንዱ ሲጎዳ ግን ጉዳቱ የሁሉም ስለሚሆን፣ የጋራ ጥላን መጠበቅ እና ማጽናት የሁሉም ወገን የተቀናጀ ርብርብ ይጠይቃል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: