ኅብረተሰቡን የሰላሙ ባለቤት በማድረግ የተጀመረው መረጋጋት ይበልጥ እንዲጸና ከፍተኛ ሥራ እንደሚጠበቅ የትግራይ ክልል የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር የኢኮኖሚና መልሶ ግንባታ ዋና አስፈጻሚ ቴዎድሮስ አረጋይ ወ/ሥላሴ (ዶ/ር) ገለጹ።
ዋና አስፈጻሚው ይህን ያሉት አስተዳደሩ የ45 ቀናት የሥራ አፈጻጸም ግምገማውን ዛሬ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ባካሄደበት ወቅት ነው።
አስተዳደሩ ለስድስት ወራት የታቀዱ ተግባራትን ለማሳካት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ቴዎድሮስ፣ ባለፉት 45 ቀናት በመጀመሪያው ምዕራፍ የሰላም እና ጸጥታ ሁኔታን የማረጋጋት እና አስተዳደራዊ መዋቅሩን ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ የመመለስ ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል።
በዞን እና በወረዳ ደረጃ አመራሮች ተመድበው አስተዳደራዊ ሥራዎች እንዲቀጥሉ መደረጉን ገልጸዋል።
ጉዳት የደረሰባቸው ቢሮዎች እና የሥራ ቦታዎችም መካከለኛ ጥገና ተደርጎላቸው ተቋርጦ የነበረው የፐብሊክ ሰርቪስ፣ የትምህርት፣ የጤና እና የማኅበራዊ አገልግሎት ሥራዎች ተጀምረዋል።
ከሰላምና ጸጥታ አንጻር የነበሩ ከፍተኛ ሥጋቶችን በመቅረፍ ኅብረተሰቡ ያለሥጋት እንዲንቀሳቀስ መደረጉን ዋና አስፈጻሚው አስረድተዋል።
ተቋርጠው የነበሩ የንግድ እንቅስቃሴዎች እና የነዳጅ አቅርቦት ወደ ክልሉ እንዲገቡ በማድረግም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን የማነቃቃት ሥራ መከናወኑን አብራርተዋል።
በክልሉ የተከሰተውን ከባድ ድርቅ ለመቋቋም ሰብዓዊ እርዳታ ለተጎጂዎች እንዲደርስ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
የመንግሥት ሠራተኞች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ገብተው ደመወዛቸው እንዲከፈል ማድረግ፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው መመለስ፣ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቱን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዲሁም በመንገድ፣ በመብራት እና በቴሌኮም መሠረተ ልማቶች ላይ የደረሰን ውድመት ጠግኖ ወደ አገልግሎት መመለስ ቀጣይ ተግባራት መሆናቸውን አብራርተዋል።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: