Search

በኢትዮጵያ በዓመት እስከ 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ለማምረት የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

ሓሙስ ነሐሴ 22, 2017 110

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ በዓመት እስከ 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ለማምረት የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ አደረጉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው፤ ዛሬ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና በዳንጎቴ ግሩፕ መካከል የማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ የድርሻ ስምምነት ፈርመናል ብለዋል።

ወደ ምግብ ዋስትና እና የግብርና ሽግግር በምናደርገው ጉዞ አንድ ሌላ እጥፋት ላይ በመድረሳችን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ እንኳን ደስ አለን ሲሉም ገልፀዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ፕሮጀክቱ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የሚፈስበት መሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአመት እስከ ሶስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ የሚያመርት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ይኽም ኢትዮጵያን ከአለም ግንባር ቀደሚ አምራቾች አንዷ ያደርጋታል ነው ያሉት።

ፕሮጀክቱ በሀገር ውስጥ የሥራ እድል እንደሚፈጥርና ለዘመናት ለተፈተኑት ገበሬዎቻችን አስተማማኝ የማዳበሪያ አቅርቦት ያረጋግጣል ሲሉም አክለዋል።

ለምግብ ሉዓላዊነት መንገዳችንም ወሳኝ ርምጃ መውሰዳችንን ያመላክታል ብለዋል።

በመላው አኅጉሩ ኢትዮጵያ ያላትን ተወዳዳሪነት በማጠናከር ሕዝባችንን እና ነጋችንን የሚጠቅሙ ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንቶችን የመከወን ጽኑ አቋማችንን ያሳያል ሲሉም ገልፀዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የዛሬውን የፊርማ ስምምነት ተከትሎ ፋብሪካው በሚቆምበት ስፍራ ፕሮጀክቱን በይፋ የምናስጀምር ይሆናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይኽን ታሪካዊ ጉዞ ጀምረናል ብለዋል።

ለገበሬዎቻችን፣ ለኢኮኖሚያችን እና ለኢትዮጵያ ነገ ስንል እንጨርሰዋለን ሲሉም ገልፀዋል።

#ebc #ebcdotstream #Ethiopia AbiyAhmedAli #DangoteGroup #Fertilizer