የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሔራዊ ማሕበር በ1952 ዓ.ም የተመሰረተ ተቋም ሲሆን፤ በመላው ሀገሪቱ ከ17 ሺ በላይ አባላት እና 31 ቅርንጫፎች እንዳሉት ታሪኩ ያስረዳል።
ብሔራዊ ማሕበር ታዲያ በየወሩ መጨረሻ ቅዳሜ ዕለት ፈለገኪን የተሰኘ የስነ-ፅሑፍ እና የሙዚቃ መሰናዶን ያዘጋጃል።
ከተጀመረ አንድ ዓመት የሞላው መሰናዶው በዛሬው ዕለትም ወርሃዊ መሰናዶው ተካሂዷል።

በዕለቱም ለአንጋፋዋ ጋዜጠኛ እና ደራሲ የምወድሽ በቀለ የሕሊና ፀሎት በማድረግም ነበር መሰናዶው የተጀመረው።
በኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሔራዊ ማሕበር ጽ/ቤት የሚቀርበው ፈለገኪን የተሰኘውን የስነ-ጽሁፍ እና የሙዚቃ መሰናዶ አካል ጉዳተኞች ተሰጥዖአቸውን ለማሳደግ የሚረዳ በመሆኑ በርካቶች ሊሳተፉበት እንደሚገባም ነው የተመላከተው።
በፕሮግራሙ የሙዚቃ እና የግጥም ሥራዎች እንዲሁም ጥናታዊ ፅሁፍ የቀረበ ሲሆን፤ ጥሪ የተደረገላቸው አንጋፋ የጥበብ ሰዎችም ተገኝተዋል።

በመርሃ ግብሩም ለማኀበሩ ድጋፍ ያደረጉ እንዲሁም ለተለያዩ አካላት ዕውቅና ተሰጥቷል።
ማሕበሩ ላለፉት 65 ዓመታት የአይነ ስውራን ሰብዓዊ፣ ማኀበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ መብቶች እንዲከበሩ ለማድረግ በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መስራቱ በመድረጉ ተገልጿል።
በቢታኒያ ሲሳይ