የሁለቱ ክለቦች ተቀናቃኝነት የሚመነጭው የአንድ ከተማ ክለብ ከመሆን ነው፡፡ በማንችስተር ዩናይትድ እና ማንችስተር ሲቲ መካከል ያለው ርቀት 7 ኪሎ ሜትር እንኳን የሚሞላ አይደለም፡፡
የአንድ ከተማ ክለብ መሆናቸው ላይ ጎረቤታሞች መሆናቸው ተጨምሮበት ደግሞም ትክክለኛው ማንችስተር "እኔ ነኝ አንተ" በሚለው ሙግት ውስጥ የክለቦቹን የተቀናቃኝነት ስሜት ከፍ አድርጎት ዓመታት አልፈዋል፡፡
የሁለቱ ግንኙነት ሲነሳ የዋይኒ ሩኒ እና ሰርጂዮ አጉዌሮ ጉዳይ የሚረሳ ሊሆን አይችልም፡፡ በማንችስተር ደርቢ በፕሪሚየር ሊጉ የቀድሞው የዩናይትድ አጥቂ ዋይኒ ሩኒ እና የቀድሞው የማንችስተር ሲቲ አጥቂ ሰርጂዮ አጉዌሮ እያንዳንዳቸው 8 ግቦችን በማስቆጠር የደርቢው ከፍተኛ ግብ አግቢዎች ናቸው፡፡ ሁለቱም አጥቂዎች በደርቢው ጨዋታ ብዙ ግብ ማስቆጠራቸው ብቻ ሳይሆን የግቦቹ ጥራትም የተለዩ ናቸው፡፡

እንግሊዛዊው አጥቂ ዋይኒ ሩኒ በ2011 የውድድር ዓመት ማንችስተር ሲቲ ላይ ያስቆጠራት ግብ በክለቡ ደጋፊዎች ዘንድ ፍጹም የምትረሳ አይደለችም፡፡ 75 ሺህ ተመልካቾች በታደሙበት 158ኛው ደርቢ ሩኒ ከናኒ የተሻገረለትን ኳስ በግሩም አጨራረስ በተለምዶ አጠራር የመቀስ ምት ወይም በሌላ ስሙ (bicycle kick) ጆ ኸርት መረብ ላይ ያሳረፈበት የደርቢው የምንጊዜም ምርጥ ግብ ናት፡፡ በኦልድ ትራፎርድ በነበረው ጨዋታ ከግቧ ጥራት ባሻገር እስከ 77ኛው ደቂቃ ድረስ አንድ አቻ ለነበረው ዩናይትድ የማሸነፊያ ግብ ጭምር በመሆን ተመዝግባለች፡፡
በተመሳሳይ ሰርጂዮ አጉዌሮም በሲቲ በቆየባቸው 10 ዓመታት የዩናይትዱ ግብ ጠባቂ ዴቪድ ዴሂያ ላይ ግሩም ግቦችን አስቆጥሯል፡፡ በተለይ በ2018 በኢትሀድ በተደረገው ጨዋታ ሲቲ በጆዜ ሞሪኒሆ ይመራ የነበረውን ዩናይትድ 3 ለ 1 ባሸነፈበት ጨዋታ አርጀንቲናዊው አጥቂ ያስቆጠራት ግብ በቀዳሚነት ትጠቀሳለች፡፡ በሌላ ጨዋታ በ2013 የሊጉ መርሀግብር ከያያ ቱሬ የተቀበለውን ኳስ አራት የዩናይትድ ተከላካዮችን አልፎ ዴሂያ መረብ ላይ ያሳረፈበት የሚረሳ አይደለም፡፡

የማንችስተር ደርቢ የወቅቱ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ግን ሁለቱም ከማንችስተር ሲቲ ናቸው ኧርሊንግ ብሮውት ሃላንድ እና ፊል ፎደን፡፡ ሁለቱም እኩል 6 ግብ አላቸው፡፡
በተለይ ፕሪሚየር ሊጉን ፈጥኖ የተላመደው ሃላንድ የሩኒን እና አጉዌሮን ክብረ ወሰን የሚያሻሽልበት ሰፊ ዕድል ያለው ተጫዋች ነው፡፡ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ በመጀመርያዎቹ 100 ጨዋታዎች 88 ግቦችን በማስቆጠር የሚስተካከለው እንደሌለም አሳይቷል፡፡
በ4ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በመጭው ዕሁድ 197ኛው የማንቹሪያን ደርቢ በኢትሀድ የሚደረግም ይሆናል፡፡
በአንተነህ ሲሳይ