Search

ኢትዮጵያ 10 ሺህ ሜትርን ለ10ኛ ጊዜ ለማሸነፍ ወርቁን ካገኘች 10 ዓመት ከሆናት ኬንያ የሚደረግ ትንቅንቅ

ቅዳሜ መስከረም 03, 2018 261

አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ በሴቶች 10 ሺህ ሜትር ሦስት የወርቅ ሜዳልያዎችን በማምጣት የሚስተካከላት የለም፡፡ 

በዚህ ርቀት በመድረኩ የኢትዮጵያን ያህል የወርቅ ሜዳልያ ያለው ሀገርም የለም፡፡ ኢትዮጵያ በእንስት አትሌቶቿ 9 የወርቅ ሜዳልያ ያላት ሲሆን ኬንያ በ4 ሜዳልያዎች 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

ብርሀኔ አደሬ በ2003 የፓሪስ ዓለም ሻምፒዮና 10 ሺህ ሜትሩን ያጠናቀቀችበት 30 ደቂቃ 04.18 ሰከንድ አሁንም ድረስ የሻምፒዮናው ክብረ ወሰን ሆኖ የተቀመጠ ነው፡፡ በዓለም ሻምፒናው የርቀቱ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ምርጥ ሰዓት ባለቤቶችም ብርሀኔ አደሬ፣ ለተሰንበት ግደይ እና አልማዝ አያና ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ በበርካታ መመዘኛዎች ፍጹም የበላይ በመሆነችበት የሴቶች 10 ሺህ ሜትር ፍጻሜ በ20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ለሌላ ክብር በጀግኖች ልጆቿ ትፎካካራለች፡፡ 

በቶኪዮ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የዓለም አትሌቲከስ ሻምፒዮና ዛሬ በይፋ ሲጀመር የዓለም አትሌቲክስ አፍቃሪ በጉጉት የሚጠብቀው የሴቶች 10 ሺህ ሜትር ፍጻሜ ቀን 9 ሰዓት ከ30 ላይ ይካሄዳል፡፡

ኢትዮጵያ በመጀመርያው ቀን የመጀመርያ ሜዳልያዋን ታገኝበታለች ተብሎ በሚጠበቀው ውድድር 27 አትሌቶች ተፋጠዋል፡፡ በውድድሩ ኢትዮጵያ በብቸኝት በአራት አትሌቶች ትወከላለች፡፡ 

የ2023 የቡዳፔስ ዓለም ሻምፒዮና የርቀቱ አሸናፊ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ በቀጥታ የመሳተፍ ዕድል ባገኘችበት መድረክ ጽጌ ገ/ሰላማ፣ እጅጋየሁ ታዬ እና ፎተይን ተስፋዬ ሌሎች ለአሸናፊነት የሚፎካከሩ አትሌቶች ናቸው፡፡

ከሚሳተፉት 27 አትሌቶች ርቀቱን ከ30 ደቂቃ በታች መግባት የቻሉ አምስት አትሌቶች ያሉበት መሆኑ የውድድሩን ፉክክር በእጅጉ ፈታኝ ያደርገዋል፡፡ ከአምስቱ አትሌቶች ደግሞ ከኬንያዊቷ ቢያትሪስ ቺቤት ውጭ አራቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡

አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ በላፉት 3 የዓለም ሻምፒዮና መድረኮች ሁለት የወርቅ አንድ የብር እና አንድ የነሃስ ሜዳልያዎች ያሏት ሲሆን ዛሬ ሦስተኛውን ወርቅ ለማምጣት በምትወዳደርበት መድረክ ከኬንያዊቷ አትሌት ቢያትሪስ ቺቤት ጋር ትልቅ ትንቅንቅ እንደምታደርግ ይጠበቃል፡፡

የቡዳፔስት ዓለም ሻምፒዮና የነሃስ ሜዳልያ ባለቤቷ እጅጋየሁ ታዬ፣ ጽጌ ገ/ሰላማ እና ፎተይን ተስፋዬ በቶኪዮ ለመድመቅ የተዘጋጁ ናቸው፡፡

የፓሪስ ኦሎምፒክ የ5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ባለቤቷ ቢያትሪስ ቺቤት የ10 ሺህ ሜትር የዓለም ክብረ ወሰንን በእጇ ከማስገባቷ በተጨማሪ ምርጥ ወቅታዊ ብቃት ላይ መገኘቷ ከጉዳፍ ጋር የምታደርገውን ፉክክር ተጠባቂም እንዲሆን አድርጎታል፡፡ 

10 ሺህ ሜትርን ከ29 ደቂቃ በታች በመግባት ብቸኛዋ አትሌት ቺቤት ከቪቪያን ቺሪዮት በኋላ ኬንያ ለ10 ዓመት ያጣችውን ወርቅ ለማሳካት ትወዳደራለች፡፡ ሌላኛዋ ኬንያዊት አትሌት አግነስ ንጌቲች እና ጃን ችፕንጌቲች በትልቁ የሚጠበቁ አትሌቶች ናቸው፡፡ 

አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ በ2005 እና በ2007 ጥሩነሽ ዲባባ በተከታታይ ያሸነፈችበትን ገድል ለመድገም በጃፓን ብሔራዊ ስቴዲም ውድድሯን የምታደርግም ይሆናል፡፡ 

ሦስቱ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ትልቅ ፉክክር ያደርጉበታል ተብሎ በሚጠበቀው የ10 ሺህ ሜትር ፍጻሜ ርብቃ ቺፕቴጌይ፣ ሳራ ቸላንጋት እና ጆይ ቼፕቶይክ ዩጋንዳን የሚወክሉ አትሌቶች ናቸው፡፡

በአንተነህ ሲሳይ