Search

197ኛው የማንቹሪያን ደርቢ

እሑድ መስከረም 04, 2018 609

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሳምንቱ ትልቅ ጨዋታ ነው፡፡ ማንችስተር ሲቲ ከ ማንችስተር ዩናይትድ፡፡

ማንችስተር ሲቲ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ከተቀናቃኙ ዩናትድ ዝቅ ብሎ የደርቢውን ጨዋታ ሲያደርግ ይሄ ከ2020 በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡

በሊጉ ካደረገው 3 ጨዋታች በቶተንሀም እና ብራይተን የተሸነፈው ሲቲ ሦስት ነጥብ ብቻ ይዞ በአንድ ነጥብ ከሚበልጠው ማንችስተር ዩናይትድ ምሽት 12 ሰዓት ከ30 ላይ በኢትሀድ ይጫወታል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች ዛሬ 197ኛ የደርቢ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ሲሆን ዩናይትድ ከከተማ ተቀናቃኙ ከተገናኙባቸው ያለፉት 8 የሊግ ጨዋታዎች ያሸነፈው ሁለቱን ብቻ ነው፡፡ በአምስቱ ደግሞ ተሸንፏል፡፡

ማንችስተር ሲቲ ከገባበት የውጤት ቀውስ ለመውጣት በሚያደርገው ጨዋታ ከፒኤስጂ ሲቲን የተቀላቀለው ጣልያናዊውን ግብ ጠባቂ ጂያንሉጂ ዶናሩማ የመጀመርያ ጨዋታውን ሊያደርግ ይችላል፡፡

አሰልጣን ፔፕ ጋርዲዮላ በጉዳት ምክንያት አሁንም የጆስኮ ግቫርዲዮል፣ አቡበክር ኩሳኖቭ፣ ጆን ስቶንስ፣ ራያን አይቲ ኑሪ እና ኦማር ማርሙሽን ግልጋሎት የማያገኝ ይሆናል፡፡

የማንችስተር ዩናይትዱ አለቃ ሩብን አሞሪም ማቲያስ ኩንሀን በጉዳት ማጣቸውን ተከትሎ ስሎቬንያዊውን አጥቂ ቤንጃሚን ሼሽኮን በቋሚነት የሚያሰልፉበት ዕድል ሰፊ ሆኗል፡፡ ዲያጎ ዳሎ እና ሜሰን ማውንት ጉዳት ያለባቸው ሌሎች ተጫዋቾች ሲሆኑ ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ በዛሬው ጨዋታ ከአዲሱ ግብ ጠባቂ ሴን ላመንስ ይልቅ ባይንደርን ቋሚ እንደሚያደርጉ በሰጡት መግለጫ አሳውቀዋል፡፡

ማንችስተር ሲቲ በሊጉ ከመጀመርያ 4 ጨዋታዎች በሦስቱ የተሸነፈው ከ30 ዓመት በፊት ሲሆን በዚያ የውድድር ዓመት ከሊጉ ወርዶ እንደነበርም ይታወሳል፡፡

በአንተነህ ሲሳይ