ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲከስ ሻምፒዮና በወንዶች 10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳልያውን ካመጣች 14 ዓመታት አልፈዋል፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ በዚህ ርቀት ወርቅ የተገኘው በ2011 የዴጉ ዓለም አትሌቲከስ ሻምፒዮና በአትሌት ኢብራሂም ጄይላን ነው፡፡
በአትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ የተጀመረው የርቀቱ የወርቅ ሜዳልያ ኢብራሂም ጀይላን ላይ ቆሟል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲከስ ሻምፒዮና በወንዶች 10 ሺህ ሜትር እንደ ሴቶቹ ሁሉ 9 የወርቅ ሜዳልያ በማግኘት በቀዳሚነት ተቀምጣለች፡፡ ከዘጠኙ ሜዳልያዎች ስምንቱ ደግሞ በሁለት አትሌቶች ብቻ የተመዘገቡ ናቸው፡፡
ፈር ቀዳጁ ኃይሌ ገ/ሥላሴ ከ1993ቱ የስቱትጋርት ዓለም ሻምፒዮና እስከ 1999 የሴቪያ መድረክ በተከታታይ አራት የወርቅ ሜዳልያዎችን ወስዷል፡፡ በተመሳሳይ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከ2003ቱ የፓሪስ ዓለም ሻምፒዮና እስከ 2009 በርሊን ሻምፒዮና በተከታታይ አራት ጊዜ አሸንፏል፡፡
ኢብራሂም ጄይላንን ጨምሮ ሁለቱ ልዩነት ፈጣሪ አትሌቶች በነገሡበት መድረክ ኢትዮጵያ ከዚህ ክብር ጋር ከተገናኘች ዓመታት መቆጠራቸው የሚያስቆጭ ቢሆንም ዛሬም ለሌላ ገድል የተዘጋጁ ልጆች አሏት፡፡
እየተካሄደ በሚገኘው የቶኪዮ ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ሜዳልያ ታገኝበታለች ተብሎ የሚጠበቀው የወንዶች 10 ሺህ ሜትር ፍጻሜ ዛሬ 9 ሰዓት ከ30 ላይ ይደረጋል፡፡ ሰለሞን ባረጋ፣ ዮሚፍ ቀጀልቻ እና በሪሁ አረጋዊ በመድረኩ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ናቸው፡፡
ያለፉት ሦስት ተከታታይ የዓለም ሻምፒዮናዎች የርቀቱ አሸናፊ ዩጋንዳዊው ጆሽዋ ቼፕቴጌይ አለመኖር ውድድሩ አዲስ ሻምፒዮን የሚያስተዋውቅበትን ዕድል አግኝቷል፡፡
አትሌት ሰለሞን ባረጋ ከአራት ዓመት በፊት በተካሄደው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ለኢትዮጵያ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳልያ ያስገኘው ዛሬ በሚወዳደርበት የጃፓን ብሔራዊ ስቴዲየም ነው፡፡
በቡዳፔስት ዓለም ሻምፒዮና 3ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ሰለሞን ዛሬ በሚያደርገው ውድድር የአሸናፊነት ግምት ካገኙት አንዱ ሆኗል፡፡ የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ 26 ደቂቃ 34.93 ሰከንድ የርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቱ ነው፡፡
አትሌት በሪሁ አረጋዊ ሌላኛው በትልቁ የሚጠበቅ አትሌት ነው፡፡ የፓሪስ ኦሎምፒክ የ10 ሺህ ሜትር የብር ሜዳልያ ባለቤቱ በሪሁ አረጋዊ በቅርብ ዓመታት ባደረጋቸው ውድድሮች የርቀቱ ከባድ ሚዛን መሆኑን አሳይቷል፡፡
የበርካታ ውድድሮች ልምድ ባለቤት የሆነው ዮሚፍ ቀጀልቻም ለአሸናፊነት ይፎካከራል፡፡ በዶሃ ዓለም ሻምፒዮና 2ኛ ደረጃ የወጣው ዮሚፍ 26 ደቂቃ 31.01 ሰከንድ የግል ምርጥ ሰዓት ባለቤት ነው፡፡
በዚህ ርቀት ኬንያ ወርቁን ካገኝች 24 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዛሬው ተጠባቂ ውድድርም ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመምጣት በኢስማኤል ኪፕኩሩይ፣ ኢድዊን ኩርጋት እና ቤንሶን ኪፕላንጋት ትወከላለች፡፡
የዩጋንዳዎቹ ኦስካር ቼሊሞ እና ዳን ኪቤትን ጨምሮ በአጠቃለት 27 አትሌቶች በ10 ሺህ ሜትር ፍጻሜው የሚካፈሉ ናቸው፡፡