የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ ማለዳ በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት እና ድል አድራጊነት በነቂስ ወደ አደባባይ በመትመም ደስታዉን ለገለፀው፤ ብሔራዊ ጀግኖቹን ላመሰገነዉ መላው የአዲስ አበባ ነዋሪ በሙሉ ምስጋናዬን አቀርባለው ብለዋል።
የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የዲፕሎማሲው ማኅበረሰብ አባላት በተገኙበት ድሉ ተከብሯል ሲሉም ገልጸዋል።
መላው የከተማችን ነዋሪ ከመቀነቱ ፈትቶ ፣ ካለዉ ቆርሶ፣ የኑዛዜው አካል አድርጎ ፣ ሕፃናት እና ተማሪዎች ሳይቀሩ የከረሜላ መግዣቸውን ለግድቡ ቦንድ መግዣ አውለዋል ሲሉም አንስተዋል።

በበርካታ ዓለም አቀፍ ጫናዎች ውስጥ ቢታለፍም በደምና አጥንት መስዋትነት ገንብተዉ ለፍፃሜ ያበቁትን የሕዳሴ ግድብን ድል በታላቅ ድምቀት ተከብሯል ሲሉም ከንቲባ አዳነች አንስተዋል።
መላው የከተማችን ነዋሪዎች የሌሊቱ ቁር፣ የዛሬዉ ከባድ ዶፍ ዝናብ ሳይበግራችሁ የዘመናት የትውልዶች ትግል ዉጤት የሆነውን ድላችሁን በጋራ አክብራችኋል ፤ ለዚህ ድል ከነበራችሁ ደጀንነት አንፃር ይገባችኋ ብለዋል ከንቲባ አዳነች።
ይህ ድል የኢትዮጵያ የመቻል ማሳያ ፣ የአይቀሬዉ ብልፅግናችን ማረጋገጫ ብሔራዊ ምልክት ነው ሲሉም ከንቲባዋ ገልጸዋል።

እኛ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ቆርጠን ስንነሳ የትኛውም ተፅእኖ ሊያስቆመን አይችልም ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ በራሳችን ገንዘብ በእኛው ሠራተኞች በላብ እና በደም ዋጋ ወደ ፊት ገሰገስን ገነባነው፣ ጨረስነው፣ አስመረቅነው ሲሉም ተናግረዋል።
የሕዳሴ ግድብ የጂኦፓለቲካ ብያኔን የለወጠ የዲፕሎማሲ ኢ-ፍትሐዊ አተያይን የቀየረ፤ ለመላው የጥቁር ሕዝቦች የማንሰራራት ድልን ያበሰረ፣ አይችሉም ባዮችን ያሳፈረ እና ያስደመመ ነው ብለዋል ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
በሄለን ተስፋዬ