የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ሥራ እና ተስፋ የኢትዮጵያ ስንቅ ስለሆኑ የኢትዮጵያን ልዕልና እናውጅ፤ ከፍታዋን እናጎናጽፍ፤ በሥራ እንደግ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ለታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድጋፍ በመስቀል አደባባይ ለተሰበሰው ሕዝብ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዚዳንቱ፣ "እንኳንም ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በሀሳብ፣ በዕውቀት ተባብረን ሠራነው" በማለት ግድቡ የሀሳብ እና ዕውቀት ውጤት መሆኑን አንስተዋል፡፡
"ዘመኑ የኢትዮጵያ ነው" ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ "ለዕድገት ከሚገሠግሡ የዓለም ሕዝቦች ጋር ሰልፋችንን እናስተካክል፤ አካሄዳችንን እናሳምር" ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኢትዮጵያ የምታባክነው እና የምታጠፋው ጊዜ እንደሌላት ገልፀው፣ “በሥራችን ሳንታበይ እውነት እና ሀቅን ይዘን እንትጋ” ብለዋል፡፡
"ተስፋ የኢትዮጵያ ስንቅ ነው፤ ብርታት የኢትዮጵያ መለያ ነው" ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ፣ ክብርም የኢትዮጵያ ጌጥ ስለሆነ መጠበቅ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ያደረጉትን ሁሉ አመሰግነዋል፡፡
የሐኬት፣ የተንኮል እና የነቀፌታ አስተያየትን ንቀው ድጋፋቸውን ለሰጡ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፤ በገጠር፣ በከተማ፣ በቆላ በደጋም ያሉ ኢትዮጵያውያን ግድቡ የጥረታቸው ውጤት ስለሆነ ደስታ ይገባቸዋል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
"በዘመን ሽግግር በየደረጃው ሀሳብ ላመነጩ፣ አመራር ለሰጡ፣ የተሰናከለውን ሁሉ ላስተካከሉ፣ የተዛባውን ላቃኑ የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት በተለይም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝቡ ስም ከፍ ያለ ምሥጋናዬን አቀርባለሁ" ብለዋል።
"በወርቃማ እና ጥበብ በተላበሰው እጃችሁ ግድቡን ላነ'ፃችሁ፤ ኃያሉን የውኃ መሽከርክሪት ገርታችሁ ኃይል እንዲሰጥ ላደረጋችሁ ጠበብት፣ በድርድር ለተጋችሁ፣ በዓለም አቀፍ መድረክ እና ሚዲያ ለኢትዮጵያ ለቆማችሁ እና ለሞገታችሁ ሁሉ ከበሬታዬ ይድረሳችሁ" በማለት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በለሚ ታደሰ