የመደመር መንግሥት ያልተሄደበትን መንገድ መሄድ እንደሚመርጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ለማሳየት የሱዳንን አካሄድ እንደ ምሳሌ አንስተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ሲመጣ ሱዳን ሰላም እንደነበረች አስታውሰው፣ ሱዳናውያን በተከተሉት የተዛባ ጥያቄ እና የተዛባ ምላሽ ቀድሞ የገነቡትን ሁሉ ማፍረሳቸውን ተናግረዋል።
የመደመር መንግሥት ግን አፍርሶ በመጀመር እንደማያምን እጅግ የገዘፈውን ታላቁን ኢትዮያ ሕዳሴ ግድብ ከነስብራቱ ተቀብሎ እሴት ጨምሮ ማጠናቀቁ ማሳያ እንደሆነም ነው የጠቀሱት።
የመደመር መንግሥትን ወደ ኋላ የሚያስጉዘው ቁጭት መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፥ ይህም "ኢትዮጵያ ሁሉ እያላት ደሃ የሆነችው የት ጋር ተሰብራ ነው?" ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚገኝበት እንደሆነ ተናግረዋል።
ሌላው የመደመር መንግሥትን ወደኋላ የሚያስጉዘው የመንፈስ ቅናት እንደሆነ ጠቁመው፣ "የበለፀጉ ሀገራት ከኢትዮጵያ በምን በልጠው ነው እዚህ ደረጃ ላይ ደረሱት?" የሚለው የመንፈስ ቅናት ጥያቄ ነው ብለዋል።
የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያውያን የት ጋር ሲያንቀላፉ ነው የታለፉት? የሚለውን የሚመረምር መሆኑን ነው አጽንኦት ሰጥተው የጠቀሱት።
በዚህ ምርመራም ስብራቱ የት ጋር እንደሆነ የመደመር መንግሥት ማግኘቱን ጠቁመው፤ የመጀመሪያው የተዛቡ ጥያቄዎች ናቸው ብለዋል።
የዚህ ምክንያቱም ትክክለኛ ጥያቄ አለመጠየቅ ትክክለኛ ምላሽ የማያስገኝ በመሆኑ እንደሆነ ነው የጠቀሱት።
ሁለተኛው የስብራት ምክንያት ለተዛባው ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ የተዛባ መሆኑ እንደሆነ አንስተው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለመደው ለውጥ በነበረው ላይ እየገነቡ መሄድ ሳይሆን የነበረውን እያፈረሱ ከባዶ መጀመር የነበረ መሆኑ ለስብራቱ መንስኤ እንደሆነ ተናግረዋል።
በለሚ ታደሰ