የመደመር መንግሥት እንዴት ወደኋላ ቀረን?፤ ከዓለም ጋር የቱ ጋር ተላለፍን? ለሚሉ ጥያቄዎች ግልጽ መልስ እና መፍትሔ ይዟል ሲሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ገለፁ።
በመጽሐፉ ላይ ትንተና ያቀረቡት ሚኒስትሯ፤ መጽሐፉ ከኋላ ቀርነት በመላቀቅ ዓለም የደረሰበት ደረጃ እንዴት መድረስ እንዳለብን አመላካች ነው ብለዋል።
የመደመር እሳቤን በመተግበር እና በመደመር ላይ የተቃኘ መንግሥትን በመመስረት ሀገራችንን ወደነበረችበት የኢኮኖሚ እና የስልጣኔ ከፍታ መመለስ፤ ሕዝባችንን ደግሞ ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና ማሸጋገር ማለት ምን እንደሆነ በዚሕ መጽሐፍ በቀላል አገላለጽ ተቀምጧል ሲሉ ተናግረዋል።
በየዘርፉ አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶችን መፍጠር፤ እነዚህን የፈጠራ ውጤቶች ደግሞ በፍጥነት ወደ ሥራ ማስገባት እና እንደአስፈላጊነቱ ደግሞ የዝላይ ስልቶችን በመከተል የሀገራችንን ብልጽግና ማረጋገጥ የዚህ ትውልድ ዋነኛ ኃላፊነቱ እንደሆነም በመጽሐፉ መቀመጡን ገልጸዋል።
የመደመር መንግሥት ባለፋት ጥቂት ዓመታት ከከተማ እስከ ገጠር ተተግብሮ በተለያዩ ዘርፎች ውጤታማ ሆኗልም ብለዋል።
መጽሐፉ ከዚሕ በኋላ ለሚኖሩን ሥራዎች አጋዥ ሆኖ ያገለግላል ሲሉም የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
በሀብተሚካኤል ክፍሉ