ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቁን በማስመልከት ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፤ ሕዳሴ ኢትዮጵያዊያን በላብ እና በደማቸው ያፀኑት የወል ሃብት ነው ብለዋል።
ግድቡ ህያው የምሕንድስና ጥበብ የታየበት የመላው ኢትዮጵያውያን ቅርስ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን ከልማት ጉዞዋ የሚያግዳት ምድራዊ ኃይል የለም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ታሪካዊ ጠላቶቻችንም የጠነከረውን አንድነታችንን ተመልክተው ከሚሸርቡት ሴራ ሊታቀቡ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ክብሯን እና ሉዓላዊነቷን የሚያስጠብቁ የቁርጥ ቀን ጀግኖች አሏት ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ መላው ዜጋ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት እና ለዘላቂ ሠላም ሊተጋ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በግድቡ የተገኘው ስኬት መንግሥት የዜጎችን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማረጋገጥ ለጀመረው የተቀናጀ ጥረት ተደማሪ አቅም የፈጠረ መሆኑንም አንስተዋል።
የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች በግድቡ ግንባታ ሒደት ያካበቱትን ልምድ እና ዕውቀት በሌሎችም ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይም ለመድገም ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በሰለሞን ባረና