Search

"በዓባይ ወንዝ ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም እንዲኖር የተፋሰሱ ሀገራት ከመተባበር ውጪ ምንም አማራጭ የላቸውም" - ኬንያዊ ምሁር ጆን ራኦ ንያኦሮ (ዶ/ር)

ዓርብ መስከረም 09, 2018 241

የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት በዓባይ ላይ ምክንያታዊ እና ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም እንዲኖር ከሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ከመወያየት እና ከመተባበር ውጪ ምንም ዓይነት አማራጭ እንደሌላቸው ድንበር ዘለል የውኃ አካላት ዓለም አቀፍ አማካሪው ኬንያዊ ምሁር ጆን ራኦ ንያኦሮ (ዶ/ር) ተናገሩ።
በሀገራቱ መካከል መቀራረብ እና መተባበር መፍጠር ከተቻለ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የጎረቤት ሀገራት ዘርፍ ብዙ ጥቅሞች አሉት ብለዋል፡፡
በዓባይ ወንዝ ላይ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ እና የግብፁ አስዋን ግድብን የመሰሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተገንብተዋል ያሉት ኬንያዊ ምሁር፤ ሀገራቱ በትብብር መስራት ከቻሉ ከሕዳሴ ግድብ ተጠቃሚ መሆን አንደሚችሉም ነው የተናገሩት፡፡
የግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሀገራትም በርካሽ ገንዘብ ጥቅም የሚሰጥ መሆኑን አንስተዋል።
ይህም የቀጣናውን ሀገራት የኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማነቃቃት የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።
የሕዳሴ ግድብ በመገንባቱ በሱዳን በየዓመቱ የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል እና የመስኖ መስመራቸው በደለል እንዳይሞላ እንደሚረዳም ምሁሩ ጠቁመዋል፡፡
የዓባይ ውኃ ከኢትዮጵያ ተነስቶ፤ ኃይል አመንጭቶ እና በሕዳሴ ግድብ አልፎ ዓመቱን በሙሉ ወደ ታችኛው የተፋሰስ ሀገራት ስለሚፈስ ሀገራቱ ለተለያዩ የልማት ሥራዎቻቸው ውኃውን በበቂ ሁኔታ እንደሚያገኙ አስረድተዋል።
የሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ሥራውን ቢቀጥልም እስካሁን በታችኛው የተፋሰስ ሀገራት ላይ ምንም ዓይነት የውሃ መቀነስ ችግር አለመታየቱ በተግባር ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
የሕዳሴ ግድብ ፋይዳ ለኢትዮጵያ ብቻ አይደለም ያሉት ምሁሩ፤ የተፋሰሱ ሀገራት መተባበር ከቻሉ ሁሉንም ጥቅሞችን በጋራ ማግኘት እንደሚችሉም አንስተዋል።
 
በላሉ ኢታላ