የከምባታ ዞን ህዝቦች የዘመን መለወጫ መሳላ በዓል በዱራሜ ከተማ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት እየተከበረ ይገኛል።
የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሣ በክብረ-በዓሉ ላይ በመገኘት መልዕክት አስተላልፈዋል።
እንደ ሀገር ከምናከብረው የዘመን መለወጫ በዓል ባሻገር የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የራሳቸውን አዲስ ዓመት ያከብራሉ ያሉት ሚኒስትሯ፤ መሳላ እና ሃምበርቾ ተራራን ጨምሮ በከምባታ ዞን የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችን ለማስተዋወቅ ይሠራል ብለዋል።
በሀገራዊው የቱሪዝም ሳምንት ከምባታ ዞንን ጨምሮ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ የቱሪስት መስህቦች እንደሚጎበኙ እና እንደሚተዋወቁም ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።
መሳላ አብሮ መብላትን ብቻ ሳይሆን በጋራ መሥራትን ጭምር እንደሚያስተምር የጠቀሱት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲ፤ በየአካባቢው ያሉ ባህሎች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ ሚኒስቴሩ ኃላፊነቱን ይወጣል ብለዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ፥ የ2018 መሳላ በዓል የሕዳሴ ግድብ በስኬት ተጠናቅቆ በተመረቀ ማግስት የሚከበር በመሆኑ ደስታችን እጥፍ ድርብ ነው ብለዋል።
አይቀሬውን የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ በመደመር እሳቤ መነሳት እንደሚገባ ጠቁመው፤ አዲሱ ዘመን ለመላው ኢትዮጵያውያን የማንሰራራት እንዲሆን ተመኝተዋል።
መሳላ ከጥንት ከአባቶቻችን ጀምሮ ሲከበር የነበረ የፍቅር፣ የዕርቅና የሰላም በዓል ነው ያሉት የከምባታ ዞን አስተዳዳሪ አረጋ እሸቱ በበኩላቸው፤ መሳላን ቂም ይዞ መሻገር ስለማይቻል በይቅርታና በአዲስ መንፈስ መሻገር እንደሚገባ አመላክተዋል።
በሲሳይ ደበበ
#Ethiopia #Kembata #NewYear #Masala