በአፍሪካ ግዙፍ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ኢትዮጵያውያን በውስጥ አቅም ብቻ ማጠናቀቅ መቻላቸው በበርካታ ዓለም አቀፍ የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች ዘንድ በአድናቆት እየተነሳ ይገኛል።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሏቸው አፍሪካውያን የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎችም ሰሞኑን ጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለራዕይ መሪ በመሆናቸው ሀገራቸው በኢንዱስትሪ የበለፀገች ለማድረግ ትልቅ ሥራ እየሰሩ ይገኛል ሲሉ ዘግበዋል።
የሕዳሴ ግድብን በመገንባት ታሪክ የሰራችው ኢትዮጵያ ጉባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባበሰሩት መሰረት የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት በዝግጅት ላይ ስለመሆኗም የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎቹ ጠቁመዋል።

ሁለት የኒውክሌር የኃይል ማመጫዎችን ለመገንባት የተደረገው ዝግጅት በሀገሪቱ የኃይል ማመንጫ ዘርፍ ስር ነቀል አብዮት የሚያመጣ የአዲስ ምዕራፍ ጅማሮ መሆኑንም አንስተዋል።
የኃይል ማመንጫው መገንባቱ ትላልቅ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ እና ጠንካራ ኢኮኖሚን ለመገንባት ያየዘችውን ውጥን ለማሳካት ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል አፍሪካውያኑ፡፡

የሕዳሴ ግድብን በቅርቡ ያስመረችው ኢትዮጵያ ተጨማሪ የኒውክሌር የኢነርጂ ተቋም ከገነባች የኃይል እጥረት ሊገትማት አይችልም ሲሉም አፍሪካውያኑ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡
አብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት በቂ የኃይል አቅርቦት ባለማሟላታቸው ትላልቅ አምራች ኢንዱስትሪዎችን መሳብ ይከብዳቸዋል ያሉት የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎቹ፤ ኢትዮጵያ ግን በቀጣይ ይህን ፈተና ማለፍ ችላለች ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለራዕይ መሪ ናቸው፤ ሀገራቸውን በኢንዱስትሪ የበለፀገች ለማድረግ ትልቅ ሥራ እየሰሩ ያሉት አፍሪካውያኑ፤ ለሀገራቸው በሚሰሩት ሥራም ትልቅ ክብር እንደሚገባቸውም የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎቹ አንስተዋል፡፡
በላሉ ኢታላ