“መስቀል በጉራጌ” ዓመታዊ ፌስቲቫል ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።
የመስቀል በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበ የዓለም የማይዳሰስ ቅርስ ነው። የመስቀል በዓል ሐይማኖታዊ ሲሆን፤ በተለያዩ ማህበረሰቦች ዘንድ መንፈሳዊ ይዘቱን ሳይለቅ በባህላዊ ኩነቶች ጭምር ይከበራል።
መስቀል በጉራጌ በሥራ ምክንያት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ርቀው የሚኖሩ የሚገናኙበት፣ በቀዬአቸው የልማት አሻራቸውን የሚያኖሩበት ታላቅ በዓል ነው ሲሉ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ገልጸዋል።
በአገር ቤትም ሆነ በከተማ የሚኖረው የጉራጌ ማህበረሰብ ለዘመናት ባዳበረው የገንዘብ እና የዓይነት የቁጠባ ሥርዓት ላይ ተመስርቶ ለወራት በበቂ ሁኔታ የሚዘጋጅበት በዓል መሆኑም አቶ ላጫ አንስተዋል።
እናቶች የመስቀል ቆጮ በመፋቅ እንዲሁም የቂቤ ‘ውጆ’ ወይም ዕቁብ በመሰብሰብ፤ ወንዶች የማገዶ እንጨትና የእርድ ከብት በማዘጋጀት፤ ወጣቶች በበኩላቸው ቤት እና አካባቢን በማስዋብ፣ ሚጥሚጣ በመውቀጥ እና ቤት በማስጌጥ የየድርሻቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ አክለዋል።
የጉራጌ ማህብረሰብ የመስቀል በዓልን ከመስከረም 12 እስከ ጥቅምት 5 ቀን ቆጮ እና ክትፎን ጨምሮ ለበዓሉ ተብለው የተዘጋጁ ባህላዊ ምግቦችና መጠጦችን ከቤተሰብ እና ከጎረቤት ጋር በጋራ እየተቋደሱ ባህላዊ ጭፈራን ጨምሮ በልዩ ልዩ ክዋኔዎች በታላቅ ደስታ ያከብሩታል።
ይህን የመሰለ የማህበረሰብ እሴትን ለማልማትና ሳይሸራረፍ ለትውልድ ለማስተላለፍ የጉራጌ እና ምስራቅ ጉራጌ ዞኖች ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ከጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ጋር በመተባበር እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል።
በሰናይት ብርሀኔ
#EBCdotstream #Ethiopia #Gurage #Meskel #Festival