የመደመር መንግሥት የትብብር ሞዴል - በኢትዮጵያ ጠንካራ የግል ዘርፍ እስኪፈጠር ድረስ መንግሥት በልማት ሥራዎች በመሳተፍ፣ ኢንቨስተር በመሆን ትልቅ ትብብር ሊያደርግ እንደሚገባ ያምናል ሲሉ በመደመር ወግ ውይይት ላይ የተሳተፉት የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ዶ/ር ፍጹም አሰፋ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን የሚመስለው የትብብር ሞዴል - የግል ሴክተሩ እና መንግሥት በቅንጅት በመሥራት በሀገር ግንባታ ላይ እንዲሳተፉ ዕድል የሚሰጥ መሆኑንም አንሥተዋል።
የመደመር መንግሥት የግል ዘርፉን ልማታዊ ወይም ኪራይ ሰብሳቢ በማለት መፈረጅ ሳይሆን ጠንካራ እንዲሆን በትኩረት የሚሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
ጠንካራ የግል ዘርፍ እስኪፈጠር ድረስ መንግሥት "ንቁ ኢንቨስተር" እንዲሆን በተቀመጠው አቅጣጫ በቱሪዝም፣ በኃይል አቅርቦት፣ በመንገድ፣ በቴሌኮም እና በሌሎችም የመሠረተ ልማት ዘርፎች ትላልቅ ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉን ለአብነት አንሥተዋል።
መንግሥት ትልቅ ኃላፊነት ወስዶ ቀዳሚ ኢንቨስተር የሚሆንባቸው ስትራቴጂክ ጉዳዮችም አሉ ያሉት ሚኒስትሯ፣ በተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም “ዓለም በፈራው መጠን ልክ ሳንገራገጭ በሬውን ቀንዱን ይዘን መሻገር ችለናል" ሲሉ ገልጸዋል።
በመደመር መንግሥት የቆዩ የኢኮኖሚ ስብራቶችን መፍታት ያስቻለ መጠነ ሰፊ ሪፎርም ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።
በላሉ ኢታላ