ኢትዮጵያውያን በቅኝ ግዛት እንዳለመገዛታችን በራሳችን እሳቤ የራሳችንን መስመር የማቅናት ዕድል አለን ይላሉ የፍልስፍና መምህሩ ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር)።
ዶክተር ዳኛቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አራተኛ መጽሐፍ በሆነው “የመደመር መንግሥት” መጽሐፍ ላይ ባተኮረው እና በኢቢሲ በቀረበው የመደመር ወግ ውይይት ላይ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።
በንግግራቸውም፣ “አንድ መሪ ሕዝቡን የሚያበረታታ መሆን፣ በይቻላል መንፈስ መገፋፋት እና የተለየ መንገድን ማሳየት እንዳለበት አንሥተው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት መጽሐፋቸው ይህን እያደረጉ ነው ብለዋል።
የመደመር ፅንሰ ሐሳብ ጽንፈኝነትን በማራገፍ ወርቃማውን አማካይ ይመርጣል ያሉት ዶክተር ዳኛቸው፣ ብዝሃነትን የሚጨፈልቅ ሳይሆን እውቅና የሚሰጥ መሆኑን አንሥተዋል።
ለብዙ ዓመታት የተኛን ሰዎች ስለሆንን በሩን አንኳኩቶ የሚቀሰቅሰንም ሰው ያስፈልጋል ያሉት የፍልስፍና መምህሩ፣ አዲሱን ትውልድ በይቻላል መንፈስ መገፋፋትም ተገቢ ነው ብለዋል።
የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ዳግማዊ ዓድዋን በሕዳሴ ግድቡ ያሳካው ትውልድ በቀጣይ የባሕር በር ባለቤትነትን እና የአቶሚክ ኃይል ተቋምን መገንባት እንደሚችል በግልፅ የሚያስረዳ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ በውጭ ለሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ስለ ኢትዮጵያም ሆነ ስለ የመደመር መንግሥት ትክክለኛ ግንዛብ ለመፍጠር ትክክለኛ መረጃ እና ትንታኔ መስጠት ተገቢ እንደሆነም ነው የተናገሩት።
በላሉ ኢታላ