Search

በመደመር መንግሥት መጽሐፍ ውስጥ የተገለጸው ‘ሐሳብ አልባ ፖለቲካ’ ምንድን ነው?

ረቡዕ መስከረም 14, 2018 128

በመደመር ወግ ላይ ሐሳባቸውን የሰጡት የፍልስፍና መምህሩ ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት መጽሐፍ ብያኔ መሰረት ‘ሐሳብ አልባ ፖለቲካ’ ማለት የፖለቲካ ሥልጣንን ለሕዝብ ጥቅም ሳይሆን ለግል ጥቅም ማዋል ነው ይላሉ።
በመጽሐፉ እንደተገለጸው፣ ‘ሐሳብ አልባ’ ማለት እንደ ፍልስፍናው “የማይጨበጥ ወይም ሐሳብ ማጣት” ሳይሆን ተቋም እንዳይገነባ ተቧድኖ መዝረፍን የመሳሰሉ ስብራቶችን የሚመለከት መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ወደፊትም ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዳትሄድ የሚበጠብጠው ይህ አይነቱ አፍራሽ አካሄድ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአመራር ቆይታቸው በተረዱት መሰረት ገልጸውታል ሲሉ ዶክተር ዳኛቸው ተናግረዋል።
የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋም (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ያልሰከነው በሐሳብ አልባ ፖለቲካ እንደሆነ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተዋንያን የፖለቲካ ገበያውን ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው ለዚህ ማሳያ መሆኑን እና ይህም ለአጠቃላይ የኢትዮጵያ ችግር መንሥኤ እንደሆነ ገልጸዋል።
ይህ ሊፈታ የሚችለው ደግሞ ሥርዓት በመገንባት እንደሆነ የጠቆሙት ዶክተር ፍጹም፣ ለዚህ ደግሞ በሐሳብ አልባ ፖለቲካ ተነድተው አቅጣጫ የሳቱትን ቅድሚያ ለሰላም በሰጠ አካሄድ ወደ መሥመር መመለስ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
"ሥርዓት ሲገነባ ሥልጣን ከሰው እጅ ይቀማ እና ለሥርዓት ይሰጣል" የሚሉት ሚኒስትሯ፣ ይህ አካሄድ የሐሳብ አልባ ፖለቲከኞችን ገበያ ስለሚያደርቅ አይፈልጉትም ብለዋል።
አሁን ግን ወደዚያ መሔድ ግድ መሆኑን እና መንግሥትም በዚህ ቀና መንገድ እየሄደ እንደሆነም አመላክተዋል።
የማኅበራዊ ሚዲያ መስፋፋት ለሐሳብ አልባ ፖለቲካ የተመቸ ሜዳ መፍጠሩን የጠቀሱት የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ዘሪሁን ተሾመ በበኩላቸው፣ እነዚህ ሐሳብ አልባ ፖለቲከኞች ለሐሳብ አልባ ፖለቲካ ገበያቸው ዘጠኝ ሰው ዳነ ከማለት አንድ ሰው ሞተ ማለትን እንደሚመርጡ ገልጸዋል።
ይህ አካሄድ ደግሞ ኢትዮጵያ ወደፊት እንዳትሄድ ያሰራት እንደሆነ አውስተው፣ "እየሞትን ከምንተጋገል እየኖርን በሐሳብ መታገል ለምን አንመርጥም?" በማለት ሐሳብ አልባ ፖለቲካ ወዳሰቡት ፍጻሜ እንደማያደርስ አስረድተዋል።
 
በለሚ ታደሰ