በሕክምና አንድ ልጅ ጤነኛ ነው ለማለት ሲወለድ ቢያንስ 2.5 ኪሎ ግራም መመዘን አለበት፡፡
ቢያንስ ግን ከ1 ኪሎ አያንስም፤ ከዚህ ካነሰ ግን በሕይወት አይተርፍም፤ ቢተርፍም ዓይኑ፣ አዕምሮው እና ሳንባው በአግባቡ እንደማይሰራ የሕክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ ደህና ሆኖ ከተረፈ ግን ተዓምር ይባላል ይላሉ፡፡
በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ አበበች ጎበና የእናቶችና ሕጻናት ማዕከል ውስጥ 900 ግራም ሆኖ የተወለደው ሕጻን ግን አነጋጋሪ ሆኗል፡፡
እናትም ያለጊዜው በ26 ሳምንት ከ6 ቀን ያለጊዜው ልጇን ልትገላገል ችላለች፡፡ ይህም በተለያየ አጋጣሚ እንደሚፈጠርም የሕክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
ከተወለደ ሁለት ወራት ያለፈው ሕፃን በቂ የሕክምና ክትትል ሲሰረግለትም ቆይቷል። አሁን ላይ ሕፃኑ በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛል ብለዋል የሕክምና ባለሙያዎች።
የካቲት 12 ሆስፒታል አበበች ጎበና የእናቶች እና የሕጻናት ሆስፒታል ዳይሬክተር እና የሕጻናት ሕክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ዱረቲ ጀማል ከኢቢሲ ዶት ስትሪም ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ አንዲት እናት ትክክለኛ የመውለጃ ጊዜዋ ከ37 እስከ 42 ሳምንት ነው ይላሉ።
ከዚህ ጊዜ ቀን በታች ሲወለድ የሕፃኑን ጤና ውስብስብ እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡
ጨቅላ ሕጻኑ ግን ሲወለድ 900 ግራም የነበረው ሲሆን፤ የእናት ጡት ወተት ባለማግኘቱ ምክንያት ክብደቱ ወደ 765 ግራም ቀንሶም እንደነበር አስታውሰዋል።
ያለጊዜ የሚወለዱ ሕጻናት የመተንፈሻ አካላቸው ሳይጎለብት በመሆኑ የሚወለዱት ሕጻኑ በራሱ መተንፈስ ባለመቻሉ በማሽን እየታገዘ እንዲተነፍስ መደረጉንም ነው ያነሱት፡፡
ያለጊዜያቸው የሚወለዱ ሕጻናት ውስብስብ ነገሮች ስለሚያጋጥማቸው የእይታ ብርሃናቸውን እስከማጣት ይደርሳሉ፤ በመሆኑም ይህ ክስተት እንዳይፈጠር ለጨቅላ ሕጻኑ በቂ ሕክምና ተደርጓል ሲሉም አስረድተዋል።
ወላጅ እናቱ 2 ወር ሙሉ በሆስፒታሉ ተኝታ፤ በደረቷ በማቀፍ እንድትንከባከበው መደረጉንም አንስተዋል፡፡
ሆስፒታሉ የሰጠው ከፍተኛ ክትትል ውጤታማ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ዱረቲ ጀማል ፤ ይህም በመንግሥት ሆስፒታል እየተሰጠ ያለው ሕክምና ምን ያህል እየተሻሻለ ያሳያል ይላሉ፡፡
ተመሳሳይ ሕክምናዎች እስከ 2 ሚሊዮን ብር የሚፈጁ መሆናቸውን አንስተው፤ አገልግሎቱ በነጻ መቅረቡም ለዜጎች አዋጭ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አሁን ላይ ሕጻኑ 1.6 ኪሎ ግራም እንደሚመዝን እና ወተት መጥባት መጀመሩን አንስተው፤ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
ጨቅላ ሕጻኑን ከሆስፒታል በማውጣት ከእናቱ ጋር ወደቤታቸው ለመሸኘት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በሜሮን ንብረት