Search

ቀጠሮ የማያዛንፉት የመስቀል ስጦታዎች የት ነው የሚደበቁት?

ዓርብ መስከረም 16, 2018 117

የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከአሮጌ ወደ አዲስ መሸጋገሪያ በመሆኑ እንኳን ሰው ተፈጥሮም ደምቃ ነው የምትታየው።
ታዲያ ከዚህ የአዲስ ዘመን ብስራት ውስጥ ሁሌም የማይቀሩት ምሥጢረኞቹ የመስቀል ወፍ እና የአደይ አበባ ቀጠሯቸውን ሳያዛንፉ በመስከረም ብቅ ሲሉ ከአስገራሚው ውበታቸው ጋር ነው።
የመስቀሏ ወፍ ላባዋን እንደምትቀይረው ኢትዮጵያውያንም ራሳቸውን አንጽተው ለቀጣዩ ፍሬያማ ጉዞ ይዘጋጃሉ። ምድር በዐደይ አበባ እንደምታጌጠው ኢትዮጵያውያንም በፀዓዳ ልብሶቻቸው ያጌጣሉ።
መስከረም እና መስቀልን ኢትዮጵያውያን ደመራ ደምረው ሕብራቸውን ያደምቁበታል፤ ችቦ አብርተው መፃኢ ብርሃናቸውን ያዩበታል። ይህ ተፈጥሮን የተከተለ አከባበር በውስጡ በርካታ ምሥጢሮችን የያዘ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሀብትም ነው።
መስቀል ሲመጣ ቀጠሯቸውን የማያዛንፉት የመስቀል ወፍ እና የአደይ አበባ ደግሞ የኢትዮጵያ ተስፋ ብስራት አድማቂዎች ናቸው። ባለ ቅኔው መንግሥቱ ለማ፡-
የመስቀል ወፍ እና ዐደይ አበባ፣
ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ፤
ማን ያውቃል….? በማለት የሁለቱ የማይዘነፍ ቀጠሮ ምሥጢር እንደሆነ ተቀኝተዋል።
እነዚህን በመስከረም ብቻ ደምቀው የሚከሰቱት ባለ ቀጠሮዎች ፍጥረታት የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ምሥጢሮች ብንላቸው የሚገባቸው ነው።
የመስቀል ወፍ እና የአደይ አበባ ከመስከረም በፊትም ሆነ ከመስከረም በኋላ አይታዩም። በእርግጥ የመስቀል ወፍ የምንላት ሁሌም አብራን የምትኖር ቢሆንም ቀለሟ የሚቀየረው ግን በመስከረም ብቻ ነው። እናም ሁለቱም ፍጥረታት አስቀድመው በነሐሴ አይከሰቱም፣ ዘግይተው በጥቅምት አይታዩም። እኛ በመስከረም እናያቸዋለን እንጂ ሁሌም አብረውን መኖራቸው ደግሞ ሌላው ምሥጢራቸው ነው።
የዐደይ አበባም ቀድሞ በነሐሴ አይከሰትም፤ ዘግይቶም በጥቅምት አይታይም። ለዚህም ነው አብዬ መንግሥቱ የመስቀል ወፍ እና የዐደይ አበባን አብሮ መከሰት እንደ ተፈጥሮ ምሥጢር አድርገው የሚያጠይቁት።
የዐደይ አበባ ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ እየደረቀ ሲሄድ ምንም ፍሬ ያለው አይመስልም፤ ከዚያ በኋላ ቅጠሉ እንኳን በምድር ላይ አይታይም። በጋውን ሙሉ እየዘነበ ከርሞ በሚያዝያ ወይም ግንቦት ብራ ቢሆን ወይም ከዚያም አልፎ ሐምሌ እና ነሐሴ ላይ ብራ ቢሆን አደይ አበባ ያለ ጊዜው አይታይም።
የመስቀል ወፍም እንዲሁ ከመስከረም ውጭ ያሉ ወራት ላይ ከመስከረም ጋር ተመሳስለው ቢመጡ እንደ መስቀል ጊዜ አትከሰትም (የላባዋን ቀለም አትቀይርም)።
መስከረም ያለውን ስሜት የትኛውም ወር አይኖረውም። በዚህ ወር የሚታዩ የተፈጥሮ ክስተቶች በጣም ልዩ ናቸው። አደይ አበባ ጋራ ሸንተረሩን በቢጫ ልብሱ ሲያጌጥ፣ የመስቀል ወፍ ደግሞ ጎጆዋን ሠርታ ሽር ጉድ ስትል ልዩ ሕብር ይፈጥራሉ። የእነዚህ ብርቅዬዎች መከሰት ከጠራው ሰማይ ጋር ሲዋሃድ ነፍስን በሀሴት ይሞላል።
በለሚ ታደሰ