Search

ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ያስመዘገበችው የመጀመሪያው የማይዳሰስ ቅርስ - የመስቀል በዓል

ዓርብ መስከረም 16, 2018 146

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሣይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ካስመዘገበቻቸው 6 የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል የመጀመሪያው የመስቀል በዓል ነው፡፡
የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በተለይም በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በድምቀት የሚከበር የአደባባይ በዓል ነው።
በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን የሚከበረው በዓሉ፣ በበርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በዋዜማው ደመራ በመደመር እና በማብራት በተለያዩ የሃይማኖቱ ሥርዓቶች የሚከበር ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ደመራው በዕለቱ ይበራል፡፡
በዓሉ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የመጣ፣ በሀገሪቱ ማኅበራዊ አንድነትን እና የእርስ በርስ ትስስርን የሚፈጥር ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶችን የያዘ ነው።
የመስቀል በዓል ለረጅም ጊዜ ተለያይተው የቆዩ ቤተሰቦች የሚገናኙበት፣ ከሀገራቸው ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር የሚመለሱበት፣ የተጣሉ የሚታረቁበት እና ሁሉም በአንድነት የሚሰባሰቡበት ነው፡፡
በ2006 ዓ.ም በዩኔስኮ የሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት በተመዘገበው በዚህ በዓል ላይ ለመታደም ከተለያዩ የውጭ ሀገራት በርካታ ጎብኝዎች ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ፡፡
በላሉ ኢታላ