Search

የብሩህ ተስፋ ምልክቷ አደይ አበባ

ዓርብ መስከረም 16, 2018 160

ክረምቱ አልፎ፣ ደመና አዝሎ የቆየው ሰማይ ጠርቶ፣ መስኩ አረንጓዴ ሲለብስ ተፈጥሮ በራሷ ያሻገረችው አዲስ ዘመን መምጣቱን ያመለክታል።
ይህን የተፈጥሮ መልዕክት የተከተሉ ሁሉ የአዲስ ዓመት ብስራትን ለመቀበል ይናፍቃሉ።
በዚህ ሁሉ ውስጥ ፈክተው ብቅ ብቅ የሚሉት አደይ አበባዎችም አዲስ ዓመት ይዞ የሚመጣውን አዲስ ተስፋ ያበስራሉ።
የዘመን ለውጥ አብሳሪዋ የመጀመሪያዋ አደይ አበባ ስትፈካ ሁሉም የራሱን የዘመን ትዝታ ለማውሳት ወደ መስኩ ጎራ ይላል።
ወቅቱን ጠብቆ በሚለመልመው መስክ ላይ የሚገኘው የአደይ አበባ ፍካት፣ የተስፋ ብርሃን ወደ ሰዎች የመጋባት ኃይል ያለው ይመስላል።
ለመሆኑ መስከረም ሲመጣ በተለይ በተራሮች አካባቢ በተፈጥሮ የምታብበው አደይ አበባ ምንድን ናት?
“እናት አበባ” እየተባለች የምትጠራው አደይ አበባ የ“ባይደንስ ማክሮፕቴራ” እፅዋት ዝርያ ውስጥ ትመደባለች።
በአፍሪካ 64 ዓይነት የአደይ አበባ ዝርያዎች እንዳሉ ይነገራል፤ ከዚህ ውስጥ ወደ 20 የሚሆኑት ዝርያዎች ደግሞ በኢትዮጵያ የሚበቅሉ ናቸው።
አደይ አበባ ለ9 ወራት መሬት ላይ ዘሩ ይቆይና በሰኔ እና ሐምሌ ወር መብቀል ይጀምራል። በመስከረም መስኩ፣ ጋራው፣ ሸንተረሩን ሁሉ ያስጌጠዋል።
አበቃቀሉም በዋናነት ተራራማ ወይም ደግሞ ኮረብታማ ቦታዎች ላይ የሚበቅል ሲሆን፤ ለዐይን ማራኪ እንዲሁም ጥሩ መዓዛ ያለው ለምለም አበባ ነው።
ፈረንጆቹ “Ethiopian Meskel Daisy” እያሉ የሚጠሩት አደይ አበባ ሀገር በቀል እፅዋት ሲሆን፤ የዘመን መሻገርን የሚያመለክት የተፈጥሮ ገጸ በረከት ነው።
ከዚህም ባለፈ ለመድኃኒትነት መዋል እንደሚችል በሳይንሳዊ ሆነ በሀገርበቀል እውቀት ስለመረጋገጡ ይገለጻል።
በተለይም የሀገር ባህል መድኃኒት ቀማሚዎች የአበባውን ቢጫ ክፍል ወስደው በማድረቅ እና ወደ ዱቄትነት በመቀየር ከማር ጋር ተለውሶ የፊት ቆዳ በመቀባት የተለየ ጥቅም እንደሚሰጥ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በመሐመድ ፊጣሞ