የመስቀል ደመራ በዓል ኢትዮጵያ በዓለማቀፍ ደረጃ በማይዳሰስ ቅርስነት ካስመዘገበቻቸው መካከል አንዱ ነው። በዓሉ በመላው ኢትዮጵያ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተወራረሰ ተጠብቆ የቀጠለ ክዋኔን የሚያሳይ የኢትዮጵያ ብዝኃነት እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ማሳያ ነው።
በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውም ይህን ነባር የአከባበር ትውፊቱን ይዞ እንዲቀጥል፤ ከኢትዮጵያ አልፎ የሰው ልጆች ኹሉ የጋራ ቅርስነቱ እንዲጠበቅ ለማስቻል ነው።
ኢትዮጵያውያንም የመስቀል ደመራ በዓልን በየዓመቱ ጥንታዊነቱንና ማኅበራዊ እሴቱን ጠብቀው ያከብሩታል። መንግሥት ልዩ ትኩረት ከሰጣቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች አንዱ ለኾነው የቱሪዝም ዕድገትም የራሱን ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
የዘንድሮውን የመስቀል ደመራ በዓል የምናከብረው ደግሞ ኢትዮጵያውያን በጋራ ያሳካነውን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድልን እያከበርን ባለንበት ወቅት ነው። ይህም በዓሉን የበለጠ ደማቅ ያደርገዋል።