ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች፤ እንኳን ለደመራ እና መስቀል በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
ብርሃነ መስቀሉ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሻገርን፣ ከፈተና ወደ ድል መጓዝን ማብሰሪያ ምልክት ሲሆን፤ ደመራው ፈታኙን ወቅት የመሻገራችን ብስራት፤ የመጪው የብሩህ ተስፋ ስንቅ ምልክት ነው።
የዘንድሮውን የመስቀል በዓል የምናከብረው ታላቁ የህዳሴ ግድባችንን በህዝባችን የተደመረ አቅም በድል አጠናቀን፤ በስኬት ከተስፋ ወደ ሚጨበጥ ብርሃን በመሸጋገር መፃዒ የኢትዮጵያን የንጋት ዘመን በተጨበጠ ብርሃን ተሞልተን ባበሰርንበት ታሪካዊ ወቅት ላይ መሆኑ ለየት ያደርገዋል።
የመስቀሉን ብርሃን በልቦናቸው አኑረው ተስፋ ሳይቆርጡ የጸኑ፤ የብርሃነ መስቀሉን መገኘት ለዓለም እንዳበሰሩ ሁሉ፤ ጊዜያዊና ወቅታዊ ችግሮችንና ተለዋዋጭ ፈተናዎች በጽናት በመሻገር በኅብረትና በትብበር ለድል መብቃት እንደምንችል በማሰብ በጋራ ለሰነቅነው የብልጽግና ትልም ስኬት በጽናት መነሳት ይኖርብናል።
በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነት እና የአንድነት እንዲሆን መልካም ምኞቴን ለመግለጽ እወዳለሁ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ