Search

ሀገራት በቀይ ባሕርና በህንድ ውቅያኖስ ላይ ፍትሐዊ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይገባል - ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ

ዓርብ መስከረም 16, 2018 33

ሁሉም ሀገራት በቀይ ባሕር እና በህንድ ውቅያኖስ ላይ ፍትሐዊ የተደራሽነት እና የተጠቃሚነት ዕድል ሊኖራቸው እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ጥሪ አቀረቡ፡፡
ፕሬዚዳንቱ በ80ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በነሐሴ ወር በተካሄደው የባሕር በር የሌላቸው ዐዳጊ ሀገራት ስብሰባ ላይ ያንጸባረቁት ሀሳብ አሁንም ሊተኮርበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ዋና ፀሐፊው በኮንፈረንሱ ወቅት "የትኛውም ሀገር በመልክዓ ምድራዊ ሁኔታ ምክንያት ከልማት፣ ኢኮኖሚ እና ቴክኖሎጂ ውጭ መሆን የለበትም" ሲሉ ማንሳታቸውን ያስታወሱት ፕሬዚዳንት ታየ፤ ጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አስታውቀዋል።
በአፍሪካ ሁለተኛዋ በርካታ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የባሕር ላይ የንግድ እንቅስቃሴን እንደምታከናውን አንስተዋል።
በመሆኑም ቀጣይነት ላለው ዕድገቷ እና ለአስተማማኝ ደኅንነቷ የቀይ ባሕር እና የህንድ ውቅያኖስ የባሕር ዳርቻዎች ለኢትዮጵያ ወሳኝ እንደሆኑ ይታመናል ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
የዓለም አቀፍ ሕግ ዋነኛ ዓላማ ለሰው ልጅ የጋራ ዕድገት እና እኩል ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ ከሌሎች ጋር በመተባበር ከሃብቶቻችን ተጠቃሚ እንድንሆን በሕጉ ተግባራዊነት ላይ ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
"ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር እና በህንድ ውቅያኖስ ዙሪያ በሚገኙ ሀገራት ሁሉ ፍትሐዊ ልማት እና አስተማማኝ ደኅንነትን ለማረጋገጥ ሁሉን አቀፍ አካሄድን መከተል እንደሚገባ ታምናለች፤ ለዚህም እየሠራች ነው" ሲሉ አስረድተዋል።
 
በላሉ ኢታላ