የመስቀሉ መልዕክት የሰው ልጆችን ሁሉ በሰላም፣ በእኩልነት እና በአንድነት ማኖር መሆኑን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ገለጹ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በመስቀል አደባባይ በደማቅ የተከበረ ሲሆን ቅዱስነታቸው የደመራ ማብራት ሥነ-ሥርዓቱን አስጀምረዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ በበዓሉ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የመስቀሉ ቃል ማለት ይቅርታን እና ዕርቅን፣ እኩልነትን እና አንድነትን እንዲሁም ፍትሕን ማረጋገጥ መሆኑን በመገንዘብ ይገባል ብለዋል።
የመስቀል ደመራ በዓል የሚከበረው ኃይለ እግዚአብሔርን ለማሰብ እና የመስቀሉ ኃያልነት እና አሸናፊነት በሐቅ እና ሰላም ላይ የተመሠረተ መሆኑን ለማሳየት ነው ብለዋል።
የመስቀሉ ዐበይት መልዕክቶች ሰው ሊያምንባቸው፣ ሊቀበላቸው እና ሊኖርባቸው፤ በውጤቱም በሥጋውም ሆነ በነፍሱ ሊድንባቸው እንደተሰጠ ማወቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የዘንድሮ የመስቀል በዓል አከባበር እግዚአብሔር የሰጠንን የውኃ ጸጋችንን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም በአንድነት ተባብረን ባካሄድነው ጥረት የሕዳሴ ግድባችንን አጠናቅቀን ባስመረቅንበት ማግስት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
ግድቡ ለሀገራችን ዳግም ልደትን ያበሰረ ስኬት ነው ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ በዚህም እግዚአብሔርን ማመስገን እንደሚገባን ገልጸዋል። በሥራው ላይ ታሪካዊ አሻራቸውን ያሳረፉትንም ሁሉ አመስግነዋል።
“በአዲሱ ዓመት እርስ በርሳችን ከመጠፋፋት ይልቅ በጋራ ሠርተን በጋራ የምንለማበት ጉዳዮችን ምርጫችን እናድርግ” ሲሉም አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።
በቢታኒያ ሲሳይ