በርካታ የውጭ ሀገራት ዜጎች በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተከናወኑ የደመራ ሥነ-ሥርዓቶች ላይ ታድመዋል።
በሀገር ባህል ልብስ ተውበው በባህር ዳር በተከበረው የደመራ በዓል ላይ የተገኙት የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች፣ የበዓሉ ትዕይንት ደስታን እንደፈጠረላቸው ለኢቢሲ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያዊያን የብዝሃ ባህሎች ባለቤት መሆናቸውን እንደተገነዘቡ አንስተው፤ ይህንን የቱሪዝም አቅም ይበልጥ መጠቀም እንደሚያስፈልግም ነው ያመላከቱት።


ባህርዳር ምቹ ነች፣ ነዋሪዎቿም እንግዳ ተቀባይ ናቸው ያሉት የውጭ ዜጎቹ ፤ በከተማዋ ጥሩ ጊዜን እያሳለፉ መሆኑን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ በተከናወነው የደመራ በዓል ላይ የተሳተፉ የውጭ ሀገራት ዜጎች በበኩላቸው፤ የደመራ በዓሉ ደማቅ እና ቀልብን የሚስብ እንደነበርም ነው የገለፁት።
ኢትዮጵያ ውብ ሀገር መሆኗን አንስተው፤ በዩኔስኮ የተመዘገበው የበዓሉ አከባበር ልዩ ስሜት እንደፈጠረባቸውም ነው የተናገሩት።
በበዓሉ የተመለከቱት ልዩ አለባበስ፣ ትውፊት እና ሐይማኖታዊ ስርዓት እንደሳባቸው ገልጸው፤ ይህንን የቱሪዝም ሃብት ይበልጥ መጠቀም እንደሚገባም አመላክተዋል።
በተስፋሁን ደስታ እና በሜሮን ንብረት