ኢትዮጵያ እና ጣሊያን የሽሬ እና የጎንደር ሆስፒታሎችን የጤና አጠባበቅ አገልግሎት ለማጠናከር የሚውል የ4.1 ሚሊዮን ዩሮ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱን በኢትዮጵያ በኩል የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ እና በጣሊያን በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር አጎስቲኖ ፓሌሴ ፈርመዋል።
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ አሕመድ ሺዴ፤ ስምምነቱ በተለይም በትግራይ እና በአማራ ክልሎች በግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል እንደሚጠቅም መግለፃቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
በስምምነቱ መሰረት የሚከናወኑ ሥራዎች ከ15 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሚቀርበውን የጤና አጠባበቅ አገልግሎት ለማሻሻል እንደሚያግዙ የገንዘብ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
በተለይም እናቶች በደህና እንዲወልዱ፣ ሕጻናት ሕይወት አድን እንክብካቤ እንዲያገኙ እና ተፈናቃዮች አስፈላጊውን የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ አስታውቀዋል።
በለሚ ታደሰ