ሕፃናት ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ የሚያደርግ ማንኛውም አካል በቃ ሊባል እንደሚገባ በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ ገለጹ።
ሚኒስትር ዴኤታዋ ይህን ያሉት፣ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በክልሉ በትምህርት ዘርፉ ላይ የሚታዩ ችግሮችን መቅረፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር በተካሄደ መድረክ ነው።
በዓለማችን በቴክኖሎጂ የመጠቁ ሀገራት መሠረታቸው ትምህርት መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ በክልሉ ያሉ ሁሉም ወላጅ እና አሳደጊዎች ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት መላክ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
በአማራ ክልል የትምህርት ቤቶች እና ተማሪዎች ምጣኔ አለመጣጣም፣ በተለይም በቂ የቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶች አለመኖር እንዲሁም በመምህራን አቅም ግንባታ ላይ የነበረውን ክፍተት እንደ ተግዳሮት አንስተዋል።
ይህን ችግር ለመፍታትም ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ሕፃናት በትምህርት ገበታቸው ላይ እንዲገኙ የተሠሩ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ለመምህራን የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ እና ተማሪዎች በትኩረት እንዲማሩ የተማሪዎች ምገባ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።
በአማራ ክልል የዘንድሮ የትምህት ዘመን ትምህርት የተጀመረ ቢሆንም፤ ምዝገባው እስከ መስከረም መጨረሻ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች መመዝገብ ላልቻሉ ልጆችም የማካካሻ ትምህርት የሚሰጥበት ሁኔታ እንደሚመቻች አመላክተዋል።
የተመዝጋቢዎችን ቁጥር ይበልጥ ለማሳደግ እና የተማረ ዜጋ ለማፍራት በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም ሚኒስትር ዴኤታዋ አስገንዝበዋል።
በሴራን ታደሰ