Search

የዓለማችን ምርጥ የገጠር መንደሮች

ቅዳሜ ጥቅምት 01, 2018 338

የገጠር ማኅበረሰብ ከከተሞች ባለው ርቀት አንጻር የዘመናዊ መሠረተ ልማቶች ተጠቃሚነቱ እምብዛም ነው።

በተለይም በኢኮኖሚ ባላደጉ ሀገራት የሚገኙ የገጠር መንደሮች የጤና፣ የትምህርት፣ የመገናኛ አውታሮች፣ የመብራት እና ንፁህ የመጠጥ ውኃ የማግኘት ዕድላቸው አናሳ ነው።

የተለያዩ ሀገራት መንግሥታት የሕዝባቸውን ዘላቂ እና አካታች ጥቅም ለማስጠበቅ የገጠሩን ማኅበረሰብ መንደር የማሻሻል መርሐ-ግብሮችን ነድፈው ተግባራዊ ያደርጋሉ።

የዘመናዊ የገጠር መንደር ፅንሰ-ሐሳብ ከቀላል ውበት ባሻገር ዘላቂ ልማትን፣ ዲጂታል ግንኙነትን፣ የኢኮኖሚ መሻሻልን እና ከፍተኛ የሕይወት ጥራትን ማዕከል አድርጎ የአካባቢ ባህላዊ ማንነትን ጠብቆ መልማት ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም ስኬታማ የሆኑት ዘመናዊ የገጠር መንደሮች ዋና ዓላማ ከተሜነትን ማስፋፋት ወይም የከተማ አኗኗርን ማለማመድ አይደለም።

ይልቁንስ ቴክኖሎጂን እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ልምዶችን በማዋሃድ የተፈጥሮ እና ባህላዊ ቅርሶቻቸውን እንደጠበቁ የአካባቢውን የአኗኗር በዘላቂነት ማሻሻል ነው።

በዚህ ረገድ የተጠና የገጠር መንደር ማሻሻያ መርሐ-ግብርን ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማ የሆኑ በርካታ ሀገራትን መጥቀስ ይቻላል። የእነዚህ ልዩ የገጠር መንደር በመመሥረት ውጤታማ የሆኑ ሀገራት ልምዶች ምን ይመስላሉ?

 

የአውሮፓ ስማርት እና ዲጂታል መንደሮች

በአውሮፓ ኅብረት (EU) ኢኒሼቲብ የተመሠረቱ "ስማርት መንደሮች" ኅበረቱ የገጠር አካባቢዎችን በማሻሻል ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣ ያለው ራዕይ ቁልፍ አካል እንደሆኑ ይነገራል።

የእነዚህ የአውሮፓ ኅብረት የገጠር መንደሮች ምሥረታ ዓላማ የገጠሩ ማኅበረሰብ እንደ ጤና፣ መንገድ፣ መብራት እና ሌሎች አስፈላጊ መሠረተ ልማት ተሟልቶላቸው የስማርት ቱሪዝም ማዕከላት እንዲሆኑ ማስቻል ነው።

እንደ መንገድ እና ኃይል ያሉ መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት ማኅበረሰቡ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም የሚያበረታታ ሲሆን፣ ዋና ግቡም ገጠራማ አካባቢዎችን ለመኖር እና ለመሥራት ምቹ ማድረግ ነው።

 

የቻይና "ዲጂታል መንደር" ስትራቴጂ

ቻይና የገጠር ስማርት መንደር መርሐ-ግብርን የጀመረችው እ.አ.አ በ2019 ሲሆን፣ መርሐ-ግብሩ በከተማ እና በገጠር አኗኗር መካከል ያለውን ክፍተት በማጥበብ የዲጂታል ኢኮኖሚ ወደ ገጠር ዘልቆ መግባትን ለማፋጠን ዓላማ ያደረገ ነው።

መርሐ-ግብሩ ግብርናን ዲጂታል ማድረግ፣ የሕዝብ አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ ማሻሻል፣ ምርቶችን በዘመናዊ መንገድ ወደ ገበያ ማቅረብ እና ኢ-ኮሜርስን ማስተዋወቅን ያካትታል።

 

የደቡብ ኮሪያ "የመረጃ አውታረ መረብ መንደር ፕሮጀክት"

ደቡብ ኮሪያ በጄኔራል ፓርክ ዘመን የተሳካ የገጠር መንደር ምሥረታን አካሂዳ ነበር። ይህ የመንደር ምሥረታ የበርካታ ነዋሪዎችን ሕይወት ከማሻሻሉም በላይ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት አፋጥኗል።

"የመረጃ አውታረ መረብ ፕሮጀክት" ደግሞ ቀደም ሲል የነበረውን ሞዴል የገጠር ኑሮን ጥራት ለማሻሻል የዲጂታል ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት የተገነባለት ነው።

በዚህ ሁለተኛው ዙር መርሐ-ግብር፣ ነዋሪዎች ምርቶቻቸውን በኦንላይን ለማስተዋወቅ እና ለመሸጥ የሚያስችን የዲጂታላይዜሽን ሥርዓት የተዘረጋ ሲሆን፣ ይህም የገጠሩን ማኅበረሰብ አጠቃላይ አኗኗር አሻሽሏል።

 

የሚሌኒየም መንደሮች ፕሮጀክት (በአፍሪካ)

ይህ ፕሮጀክት ከ2005-2015 ከሰሃራ በታች ባሉ 10 የአፍሪካ ሀገራት ተግባራዊ ያደረጉት ሁለንተናዊ እና ዘመናዊ የገጠር ልማት ሞዴል ነው።

ዓላማውም የገጠሩ ማኅበረሰብ ከአስከፊ ድህነት እንዲወጣ ለመርዳት ዘመናዊ ግብርና፣ ጤና፣ ትምህርት እና መሠረተ ልማት በፍጥነት መዘርጋት ነው።

 

የተመድ ልማት ፕሮግራም (UNDP) "የነገ መንደሮች" (በቱርክ)

ይህ ፕሮጀክት ሁሉን አቀፍ እና አረንጓዴ ዕድገት ላይ የሚያተኩር ፕሮጀክት ነው።

የፕሮጀክቱ ዓላማ የገጠሩን ማኅበረሰብ በዕደ-ጥበብ ሥራዎች በማሠልጠን፣ ምርታማነትን በማሳደግ እና የማኅበረሰቡን አቅም በመገንባት ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትን ማረጋገጥ ነው።

 

የተመረጡ ዘርፎች ላይ አተኩረው የተመሠረቱ የገጠር መንደሮች (በፖላንድ)

ይህ መርሐ-ግብር መንደሮች በአካባቢያቸው ያለውን አቅም መሠረት አድርገው ለዕድገታቸው የሚጠቅም ዘርፍ ላይ የሚሰማሩበት ነው።

በአካባቢያቸው በስፋት በሚገኙ እምቅ የአካባቢ ሀብት ላይ በመሰባሰብ እንደ የማዕድን መንደር፣ የዕፅዋት መንደር ተደራጅተው በዘርፋቸው ምርታማ በመሆን የሀገርን ኢኮኖሚ የሚደግፉ ናቸው።

እነዚህ መንደሮች ከተሰማሩበት ዘርፍ በተጨማሪ ቱሪዝምን ለመሳብ እና ሥራዎችን ለመፍጠር ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እና የዲጂታል መሠረተ ልማት ይዘረጋላቸዋል።

 

ሺራካዋ-ጎ እና ጎካያማ (ጃፓን)

"ጋሾ-ዙኩሪ" በሚባሉ ባህላዊ የሳር ቤቶቻቸው ዝነኛ የሆኑት እነዚህ የጃፓን መንደሮች፣ የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ እና የባህል ሕያው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሞዴል እስከመሆን ደርሰዋል።

በዚያ ያለው ዘመናዊነት ባህላዊ፣ የጋራ እና አካባቢን የሚስማማ የአኗኗር ዘይቤን በመጠበቅ የቱሪዝም ፍሰትን እና የጥበቃ ገንዘቦችን ለማስተዳደር ቴክኖሎጂን መጠቀምን ያካትታል።

 

ፔንግሊፑራን መንደር (ኢንዶኔዥያ)

ይህ መንደር የንፅህና አጠባበቅን፣ የቆሻሻ አያያዝን እና ዘላቂ ቱሪዝምን በማዋሃድ ባህላዊውን የባሊኒዝ አርክቴክቸር እና የጋራ መዋቅርን ጠብቆ የተመሠረተ ነው።

ይህ አመሠራረት እና የነዋሪዎቹ የመንደሩ አያያዝ መንደሩ እጅግ ንፁህ እና ሥርዓት ካላቸው ምርጥ መንደሮች አንዱ ያደርገዋል።

 

የገጠር ኮሪደር ልማት - ኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ የገጠር መንደሮች ምሥረታ የተጀመረው በ1970ዎቹ በደርግ መንግሥት አማካኝነት ነበር።

ዓላማው በጎ የነበረ ቢሆንም በቂ ግንዛቤ ባለመፈጠሩ ደርግ ሲወድቅ መንደሮቹም ተበትነው ነዋሪዎቹ ወደ ቀድሞ ቀዬአቸው ተመልሰዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተሞችን ማዘመን የጀመረችው ኢትዮጵያ በከተሞች የተገኘውን ልምድ ወደ ገጠርም ወስዳ እየሠራች ትገኛለች።

ይህ የኢትዮጵያ የገጠር ኮሪደር ልማት መርሐ-ግብር ገጠሩን የተሻለ ጥራት ወዳለው አኗኗር ዘይቤ የመለወጥ ጥረት ነው።

የመርሐ-ግብሩ ዓላማ የገጠር አካባቢዎችን በዘመናዊ መሠረተ ልማት በማስተሳሰር እና ማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት የተመጣጠነ ልማት ማምጣት ነው።

በዚህም መሠረት የተሻሻሉ የመኖሪያ ቤቶች፣ የመብራት፣ የንፁህ ውኃ፣ የጤና እና የትምህርት አገልግሎቶች እንዲሁም የተሻለ የገበያ ተደራሽነት ያላቸው መንደሮች ይገነባሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በዚህ መሠረት በሀላባ እና ካምባታ እንዲሁም በሀዲያ እና ስልጤ ዞኖች የተገነቡ ሞዴል መንደሮችን ለነዋሪዎች አስረክበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደነዚህ ዓይነቶቹ የገጠሩን ማኅበረሰብ ኑሮ የሚለውጡ መንደሮች በስፋት እንዲሠሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

በለሚ ታደሰ

#EBC #ebcdotstream #smartvillages #corridordevelopment