Search

የተፈጥሮ ጋዝ መጠቀማችን ከግለሰብ እስከ ሀገር ተጠቃሚ የሚያደርገን ነው - የአውቶሞቲቭ ባለሙያዎች

ረቡዕ መስከረም 28, 2018 129

የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክትን በራስ አቅም እውን ማድረግ ብሎም መጠቀም፤ ከግለሰብ እስከ ሀገር ያለ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን የአውቶሞቲቭ ባለሙያዎች ገለፁ።

የተፈጥሮ ጋዝ መጠቀም ዜጎች ለትራንስፖርት የሚያወጡትን ወጪ ከመቀነስ ባሻገር ለወጪ ንግድ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ስለመሆኑ ከኢቢሲ ኤፍኤም አዲስ 97.1 ጋር ቆይታ ያደረጉት የአውቶሞቲቭ ባለሙያ አቶ ኤልያስ የኋላወርቅ ገልፀዋል።

ለተሽከርካሪ፣ ለአፈር ማዳበሪያ፣ ለኃይል ማመንጫ እንዲሁም ለኢንደስትሪ አገልግሎት የሚውለው የተፈጥሮ ጋዝ 25 በመቶ የሚሆነውን የዓለም ሀገራት የነዳጅ ፍላጎት የሚሸፍን ነው።

ቻይና፣ ሕንድ፣ ኢራን፣ አርጅንቲና እና ፓኪስታን የጋዙ ተጠቃሚ ከሆኑ ሀገራት በቀዳሚነት የሚቀመጡም ናቸው።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያም ይህን ጎራ መቀላቀሏ የትራንስፖርት ምህዳሩን ከመቀየር ባሻገር፤ የዓየር ንብረት በጥሩ መልኩ እንዲለወጥ የሚሰራውን ሥራ የሚያጎለብት መሆኑን ባለሙያው ይገልጻሉ።

እንዲሁም በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችን ማብቃት ፣የጋዝ መሙያ ጣቢያዎችን ማመቻት እና በቂ መለዋወጫ እንዲኖር መሰራት እንዳለበት ገልፀዋል።

የተፈጥሮ ጋዝ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች የጋዝ መያዣ ታንከራቸው በየ15 ዓመቱ መቀየር እንደሚኖርበት ያስረዱት ባለሙያው፤ በትክክለኛ ባለሙያ በጥንቃቄ ከተገጠመ አስተማማኝ እና ለአደጋ የተጋለጠ እንዳልሆነ አፅዕኖት ሰጥተዋል።

በአፎሚያ ክበበው