Search

ኢትዮጵያ እና ጣሊያን የዕዳ ሽግሽግ ስምምነት ተፈራረሙ

ረቡዕ መጋቢት 09, 2018 36

ኢትዮጵያ እና ጣሊያን ስልታዊ የልማት አጋርነታቸውን የሚያጠናክር እና የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ ግብር የሚደግፍ የዕዳ ሽግሽግ ስምምነት በጣሊያን ሮም ተፈራርመዋል።
የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማገገሚያ ጥረት ለማገዝ ትልቅ ምዕራፍ ተደርጎ በሚቆጠረው በዚህ ሥነ-ሥርዓት ላይ፥ የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ እና የጣሊያን ሪፐብሊክ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር ጂያንካርሎ ጆርጌቲ ስምምነቱን ፈርመዋል።
ይህ የሁለትዮሽ የዕዳ ሽግሽግ ስምምነት በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ ስር ይፋዊ አበዳሪዎች ኮሚቴ በሚመራው ሂደት መሠረት የተከናወነ ነው።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፤ እ.ኤ.አ. በሐምሌ 2025 የተደረሰውን የመግባቢያ ሰነድ እንዲሁም አሁን የተፈረመውን የሁለትዮሽ ስምምነት በስኬት ለማጠቃለል ጣሊያን ላሳየችው ገንቢ ተሳትፎ እና አመራር ምስጋና ማቅረባቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
የጣሊያን ሚኒስትር ጂያንካርሎ ጆርጌቲ በበኩላቸው ስምምነቱ ከኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ጋር የተጣጣመ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ኢትዮጵያ ቁልፍ አጋር ሀገር በሆነችበት የጣሊያን "የማቴይ ዕቅድ ለአፍሪካ" ስኬት የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።