ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተጀመረውን የፍትህ አሰጣጥ ቴክኖሎጂ በዛሬ ዕለት ጎብኝተዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝቱ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት፤ ፍትህ የኢትዮጵያ ህዝብ ዋነኛ ጥያቄ በመሆኑ ለዚህ መፍትሄው አገልግሎቱን ማዘመን ነው ብለዋል፡፡
በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተጀመረው የፍትህ አሰጣጥ ቴክኖሎጂ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወትም ነው የገለጹት፡፡
የአገልግሎት ሥርዓቱ በሚዘምንበት ጊዜም ፖሊስ፣ አቃቤ ህግ፣ ፍርድ ቤት፣ ጠበቃ አሰራራቸው መዘመን እንዳለበት እና ዜጎች ቀልጣፋ እና ዘመናዊ፣ ፍትሀዊ የሆነ የፍትህ አገልግሎት ማግኘት እንደሚያስችላቸው አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያን ብልጽግና ስናረጋግጥ ፍትህ እና የአኗኗር ዘዴ ትኩረት የምናደርግባቸው ጉዳዮች ናቸው ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡
በሀገሪቱ ያሉ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እየዘመኑ ስለመምጣታቸው አንስተው፤ ለአብነትም የመሶብ አገልግሎት ተጠቃሽ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተጀመረው የፍትህ አሰጣጥ ቴክኖሎጂ በሁሉም ክልሎች ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዲጂታል 2025 ተጠናቅቆ ዲጂታል 2030 ሲቀረጽ ትኩረት ከተሰጠባቸው መስኮች አንዱ የፋይናንስ ዘርፉ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዜጎች የገንዘብ ዝውውር በሚያደርጉበት ወቅት ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም አገልግሎቱ ቀላል እንዲሆንላቸው ማስቻሉን ገልፀዋል፡፡
በዚህ ሂደት በቢሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ ዝውውር መደረጉን አንስተዋል፡፡
በሀገሪቱ እየተከናወነ ያለው የዲጂታላይዝድ አሰራር ጠቀሜታው በስፋት እየታየ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በሜሮን ንብረት
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #AbiyAhmedAli #Smart_Court_System