የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ፣ ነዋሪዎች የሕዝብ አገልግሎቶችን ባሉበት ቦታ ሆነው ማግኘት የሚያስችላቸውን አዲስ የበይነ መረብ (ኦንላይን) አገልግሎት ሥርዓት በይፋ ሥራ አስጀምሯል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፣ አዲሱ ሥርዓት የራስን ችግር በራስ አቅም እና በቴክኖሎጂ ለመቅረፍ እየተሠሩ ላሉ ሀገራዊ ሥራዎች በተግባራዊ ማሳያነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ዘመናዊ አሠራር ነዋሪዎች አገልግሎት ለማግኘት ወደ ተቋሙ በአካል መምጣት ሳያስፈልጋቸው፣ ባሉበት ቦታ ሆነው ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ ከማድረጉም ባሻገር፣ የራሳቸውን መረጃ በራሳቸው ማስተዳደር የሚችሉበትን ዕድል የሚፈጥር ነው።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ንጉሤ በበኩላቸው፣ ቴክኖሎጂው ዜጎች ቀልጣፋ እና ከብልሹ አሠራር የጸዳ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
አያይዘውም፣ ሥርዓቱ በተለይም የሐሰተኛ ሰነዶች ዝውውርን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።
በተጨማሪም ነዋሪዎች አገልግሎቱን በሚያገኙበት ጊዜ በግል መረጃዎቻቸው ላይ ስህተት ቢፈጠር፣ ካሉበት ቦታ ሆነው በራሳቸው ማስተካከል እንዲችሉ ሥርዓቱ ይፈቅዳል።
ይህም የተገልጋዮችን እንግልት በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ በተሻለ ምቾት አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋል።
ደንበኞች ወደ Portal.aacrrsa.gov.et ድረ-ገጽ በመግባት አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ የተገለጸ ሲሆን፣ እነዚህ እና መሰል የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንደ ሀገር የተያዘውን "ዲጂታል ኢትዮጵያ" ራዕይ እውን ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተጠቁሟል።
በብሩክታዊት ተገኝ